ሁለተኛው የአንድ ጤና (ONE HEALTH) ስትራቴጂክ እቅድ በመዘጋጀት ላይ ነው

በኢትዮጵያ የሕበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ የጤና ደንብና የአንድ ጤና ጽ/ቤት /International Health Regulation and One Health Office/ የተለየዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአጋር ድርጅት እና የሙያ ማሀበራት ተወካዮች በተገኙበት ሁለተኛውን የአንድ ጤና የእስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡
የአንድ ጤና እስትራቴጂክ እቅድ የሚዘጋጅበት ዋና ዓላማ በዋናነት ከእንስሳት እና ከአካባቢ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአንድ ጤና መርህ መሠረት ለመከላከል፤ ለመቆጣጠርና አቅም ለመገንባት ሲሆን፤ የሚዘጋጀዉም የሚመለከታቸዉን ሁሉንም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የአጋር ድርጅት አካላት በማሳተፍ ይሆናል፡፡ ይህ የጋራ ዕቅድ ለሚቀጥሉት 5 ተከታታይ ዓመታት (2025-29) የሚያገልገል ይሆናል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ መክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት በእንሰሳት እና በአካባቢ የጤና ችግሮች ምክንያት የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከምንጊዜውም በላይ የአንድ ጤና ቅንጅታዊ ስራ እጅግ ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛልን ብለዋል፡፡ አያይዘዉም በሀገራችን በዚህ ረገድ በዓለም አቀፍም ደረጃም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለመቋቋም የአንድ ጤና ትብብር እና ቅንጅታዊ ስራዎች እየተሰሩ መልካም ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፤ ዋና ዳይሬክተሩም አያይዘው የአንድ ጤና እስትራቴጅክ እቅድን ስናዘጋጅ ሳይንስን መሰረት በማድረግ መረጃን በመተንተን እና የሕብረተሰብ ጤና ውሳኔዎችን ለመስጠት በሚያስችል መልኩና የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል::
ዕቅዱም የሚመለከታቸውን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን ያካተተ ስራ ለመሰራት የሚያስችል እንዲሆን እና ለተግባራዊነቱም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ የጤና ደንብና የአንድ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት አሁን የምናዘጋጀው የአንድ ጤና እስትራቴጅክ እቅድ ከመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች እስትራቴጅክ እቅድ ጋር በማናበብ የሚዘጋጅና ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል በማለት ተናግረዋል፡፡ አያይዘዉም ይህ ሁለተኛው ዙር የእስትራቴጅክ እቅድ አሰፈላጊነት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ በሽታዎችን፣የእንሰሳት በሽታዎችንና የአካባቢ ጤና ችግሮችን የአንድ ጤናን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ሁሉም የሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የአጋር ድርጀቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች የአንድ ጤና እንቅስቃሴዎችና እየተመዘገበ ያለውን ውጤት እንዲሁም ጠቀሜታ አስመልክቶ በነበረው መድረክ ላይ የየራሳቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለእቅድ ዝግጅቱ የሚያግዙ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ የየሴክተሩ መረጃዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተጨማሪም የአንድ ጤና ወሳኝ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እስካሁን የተሰሩ ውጤታማ ስራዎች እና ተግዳሮቶች ምን ነበሩ? ለሚሉ ጥያቄዎች እና ሌሎች በእቅዱ ውስጥ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን በአተገባበር ላይ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሔቻቸው ላይም መግባባት ተደርሷል