ሁለተኛ ዙር የተቀናጀ ፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኔስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም ዓቀፍ የፖሊዮ ማጥፋት ፕሮግራም ተወካዮች፣ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች እና የአዳማ ከተማ ም/ከንቲባ እንዲሁም የአጋር ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት 2ኛውን ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በአዳማ ከተማ ግንቦት 22/2017 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የፕሮግራሙን መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት የዚህ የሁለተኛዉ ዙር የፖሊዮ የክትባት ዘመቻ በሁሉም የመጀመሪያዉ ዙር የፖሊዮ ክትባት በተሰጠባቸዉ 9 ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ከ15.3 ሚሊዮን በላይ እድሜያቸዉ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ለመክተብ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
አንደኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በዘጠኝ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ባለፈው የካቲት ወር 2017 ዓ.ም ከ15.3 ሚሊዮን በላይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የአንደኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን እና ከአጎራባች አገራት ኬንያ እና ሶማሊያ ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር በመግቢያና መዉጫ ኬላዎች ላይ በርካታ ህጻናትን መክተብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡ የሁለተኛው ዙር ክትባት ዘመቻ ከግንቦት 22-25/2017 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት በቤት ለቤት ጉብኝት እና በት/ቤቶች የሚሰጥ መሆኑን እንዲሁም ሀጻናቱ ከዚህ በፊት የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባቱን የሚወስዱ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ፖሊዮ ጨርሶ ማጥፋት ስትራተጅዎች አንዱና ዋነኛው የሆነውን የመደበኛ ክትባትን ለማጠናከር መደበኛ ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረዉ ያቋረጡ ህጻናትን የመለየትና የመከተብ እንዲሁም ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሽንትና የሰገራ መቆጣጠር ችግር (ፊስቱላ) የገጠማቸውን እናቶች የመለየት እና ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ እና የኤም ፖክስ (Mpox) የቅኝትና ምላሽ ስራዎች ከክትባት ዘመቻዉ ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚሰሩ ይሆናል።
ዶ/ር ተስፋዬ ከበበዉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ አቶ ንጋቱ ሞቱማ፡ የአዳማ ከተማ ምክትል ካንቲባ እና የአገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ፣ ፕሮፌሰር ቦጋለ ወርቁ፡ የብሔራዊ ፖሊዮ ሰርተፊኬሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የአጋር ድርጅት ተወካዮች የፓሊዮ ክትባት ዘመቻን አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡