ለሀገራዊ የምግብ ደህንነት ጥናት ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮች ለክልሎች ድጋፍ ተደረገ

ለሀገራዊ የምግብ ደህንነት ጥናት አገልግሎት የሚውሉ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮች ለክልሎች ድጋፍ ተደረገ።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እና በኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን በትብብር እየተካሄደ ላለው ሀገራዊ የምግብ ደህንነት፣ ምግብን ከባእድ ነገር ጋር መቀላቀል እና የምግብ ንጽህና አጠባበቅ ልምምድ ጥናት አገልግሎት የሚውሉ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮችን የጣሊያን መንግሥት ለክልሎች አገልግሎት እንዲውል ለኢትዯጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስረክቧል ።


ጥናቱ በጣሊያን መንግሥት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እየተተገበረ ያለ ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱ በ25 ከተሞች እየተካሄደ ነው። ለጥናቱ አፈጻጸም አስፈላጊ የሆኑት የመረጃ ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ክቡር ሴም ፋብሪዚ አማካይነት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በርክክቡ ላይ እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ደህንነትን ለማጠናከርና የምግብ ንጽህናን ለማሻሻል የሚያግዙ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ጥናቶችን በማካሄድ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች ጠቃሚ ግብዓት እያቀረበ ይገኛል።ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የጣሊያን መንግሥት በየጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) በኩል ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ይህ አጋርነት በምግብ ደህንነት ዘርፍ እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶችን ከማጠናከር ባሻገር በሌሎች የሕብረተሰብ ጤና መስኮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል።
የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በበኩላቸው የጣሊያን መንግሥት እንደዚህ ያሉ የሕብረተሰብ ጤናና የምግብ ደህንነት ፕሮጀክቶችን መደገፉን ገልጸው፣ እስካሁን በፕሮጀክቱ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ የጣሊያን መንግሥት የEPHI እና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ስራዎችን በቀጣይነት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ በበኩላቸው፣ የተደረገው ድጋፍ የጥናቱን ስኬታማ አፈጻጸም ከማገዝ ባሻገር የፌዴራልና የክልል የምግብ ቁጥጥር ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ምግብ፣ የአካባቢ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሰረሻ ተሰማ በበኩላቸው ጥረናቱ በዘጠኝ ዋና ዋና የምግብ ምርቶች ላይ የምግብ መበረዝ አስመልክቶ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በፍራፍሬና አትክልት፣ በወተት ፣ በዶሮ ስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እና በቄራዎች እንዲሁም ባለ አራት እና ከዚያ በላይ ኮከብ ባላቸው ሆቴሎች ለሚካሄደው ጥናት የተደረገው ድጋፍ እገዛ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
መርሃ ግብሩ ላይ የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) ኃላፊ ክቡር ሚካኤል ሞራን እና የኤምባሲው ልዑካን እንዲሁም የክልል ተወካዮችና የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ኃላፊዎች በኢንስቲትዩት ብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ተገኝተዋል።