ለሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ የግብዓቶች ዝርዝር መመሪያ

ለሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ የግብዓቶች ዝርዝር መመሪያ ማጠናቀቂያ አውደ ጥናት ተካሄደ
ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ፈጣን፣ የተቃነጀ እንዲሁም ሕይወት አድን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች የግብአቶች ዝርዝር መመሪያ ለማጠናቀቂያ አውደ ጥናት (ወርክሾፕ) ከግንቦት 18 – 22, 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት አስተዳደር ዲቪዥን አስተባባሪ አቶ ቢቂላ ዲሪባ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ እየተዘጋጀ ያለው የግብአት ዝርዝር መመሪያ ድንገተኛ አደጋዎች ከመከሰቱ በፊት የሚደረግ የቅድመ ዝግጁነት ስራ አካል ነው። ዋናው ዓላማው አደጋ ከመከሰቱ በፊት ለእያንዳንዱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ምን ዓይነት ግብአቶች እንደሚያስፈልጉ አስቀድሞ መለየት፣ ሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ወጥ መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለት ዘላቂነትን ማረጋገጥ ነው። አስተባባሪው አክለውም፥ ይህ ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋቱ ሊከሰቱ ለሚችሉ አደጋዎች ምላሽ መስጠ የሚያስችል ጠንካራ፣ ተቋማዊ እና ዘላቂ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት ሥርዓት መገንባት ነው።
አውደ ጥናቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት ሥርዓትን ለማዘመን፣ የግብአት ድግግሞሽ እና ብክነትን ለመቀነስ፣ ወጥ የሆነ የምላሽ ሂደት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚረዳ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም መመሪያው ተቋማት አንድ አይነት የምላሽ አሰጣጥ እንዲከተሉ በማድረግ ቅንጅታዊ አሠራር ለመፍጠር እንደሚረዳ ተመላክቷል።
በአውደ ጥናቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሕብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ WHO፣ Project Hope፣ JSI፣ UKHSA፣ CHAI፣ ከክልሎች እና ከሆስፒታሎች የተውጣጡ፣ በቀጥታ የስራው ባለድርሻ የሆኑ አካላት ተሳትፈዋል።
ይህ መመሪያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች ዝግጁነትን የሥራ ባህል ለማድረግ መሠረታዊ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።