ለዓለም ሳይንስ አስተዋጽኦ ላደረጉ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እውቅና ሰጠ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩ-የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ምግብ፣ የአካባቢ ጤናና፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ለስድስት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ባለሙያዎች የእዉቅናና የምስጋና ሽልማት መርሀ ግብር አካሄደ።
ተመራማሪዎቹ የኢትዮጵያ የምግብ ሰንጠረዥን አሻሽሎ በማውጣት፣ ለነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ጨውን በፎሊክ አሲድ ማበልጸግ ውጤታማነት ጥናት፣ በነፍሰ ጡር እናቶች ብዙ ስብጥር ያለው ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ውጤታማነት ጥናት እና የትምባሆ አጠቃቀም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምን ይመስላል (Global Tobacco Survey) በሚሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ነው እውቅና ያገኙት።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በመድረኩ ላይ ለዓለም ሳይንስ አስተዋጽኦ አድርገው የእዉቅናና የምስጋና ሽልማት የተሰጣቸውን የኢንስቲትዩቱን ስድስት ተመራማሪዎችና ባለሞያዎች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ ጥናትና ምርምሮች ከሀገር አልፈው ለዓለም ሁሉ የሚተርፉ ሲሆኑ ኢትዮጵያንም በዓለም ይበልጥ ለማስጠራት በጣም ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል በማለት ገልጸዋል።
የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ የዳይሬክቶሬታቸውን የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሲያቀርቡ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን እና ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እውቅና አግኝተው የተጀመሩ መሆናቸውን ገልጸው የተቋሙንም ስም ከፍ ያደረጉትን እውቅና የተሰጣቸውን የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችንም አመስግነዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት፣ የዳይሬክቶሬቱ የስራ ክፍል ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።