መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእዉቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ የተለያዩ ጤና ተቋማት ተወጣጥተው በ3 ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP/Field Epidemiology Training/) ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የካቲት 6/2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የእዉቀና ሰርተፍኬት በመሰጠት አስመርቋል።
አቶ ጃፈር ከዛሊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር አቅምን ለማሳደግ የመሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠናን ላለፉት አመታት ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በአጠቃላይ ስልጠናው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ ከአዲስ አበባ ለተወጣጡ ከ200 በላይ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሞያዎች ስልጠናው የተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ አወል ዳወድ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ በአራት ዙር (cohort 4) መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቀድሞ የመለየት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤ እንዲሁም መሰረታዊ የኮምፒውተር ሞያዎች ጨምሮ ለባለሙያዎች በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም በዚህ ዙር 40 ሰልጣኞች ለምረቃ የበቁ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።
የብሄራዊ ስልጠና ማዕከል ማስተባበሪያ ተወካይ አቶ አስፋዉ ወሰን የስልጠና ማዕከሉ በተመለከተ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከሉ ከህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ ለተወጣጡ “4ተኛ cohort ” ሰልጣኞች ዛሬ የምረቃ መርሐ ግብሩን ይፈፅማሉ ስለሆነም የስልጠና ማዕከሉ የስልጠና ፋላጎት ዳሰሳ እና የስልጠና ክፍተቶች ላይ ከመስራት አንስቶ የስልጠና ማንኑዋሎችን እያዘጋጀ ከሁሉም ዳይሬክቶሬች ጋር በመሆን ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ሰልጣኝ ምረቃ ድረስ ያስተባብራል ይህንን ግንባር ቀደም እየሰራ ይገኛል በማለት ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል ዳምጠው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በእዉቅናዉ ሰርተፍኬት ላይ በመገኘት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ይሄንን ስልጠና የኢትዮጵያን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በጋራ በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዉ ሰልጣኞች ከስልጠናው ባገኙት ተጨማሪ እዉቀት ማህበረሰባቸዉን በተሻለና በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።