መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ያጠናቀቁ የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ዕውቅና አገኙ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከአማራ ክልል ተውጣጥተው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠናን (Frontline-Field Epidemiology Training) ላጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ህዳር 20/2017 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ሰጠ።
“ከዚህ ቀደም በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በአምስት ዙር ስልጠናው የተካሄደ ሲሆን ይህንን ስደስተኛውን ዙር ለየት የሚያደርገው ሰልጣኞቹ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በመቋቋም በሦስት ዙር የተሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ ለምርቃት መብቃታቸው ነው፣” በማለት አቶ አወል ዳውድ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ እና የስልጠናው አስተባባሪ ገልፀው ስልጠናውን ከጀመሩት 38 ባለሙያዎች 27ቱ በመስክ የስሯቸውን የተግባር ስራዎች አቅርበውና አስገምግመው ለምርቃት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል።
ከመድረኩ መረዳት እንደተቻለው የዚህን ዙር ስልጠና ጀምረው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማጠናቀቅ ላልቻሉ ስልጠናውን የሚያጠናቅቁበት ሁኔታዎች ቀጣይ እንደሚመቻቹ ነዉ።
የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ወክለው በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ ሀብታሙ አለባቸው በበኩላቸው በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከስቱ የጤና አደጋዎች በመኖራቸው ይህን ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች ደግሞ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ጠንካራ አቅም እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
ስልጠናው ከሌሎች ተያያዥ ስልጠናዎች በተጨማሪ በዋናነት የቅኝት መረጃን (Surveillance data) በመጠቀም ወረርሽኝ (outbreak) በአንድ አካባቢ ሲከሰት ቶሎ በመለየት (detect) እና ሪፖርት የማድረግ፥ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤን ጠለቅ ባለ መልኩ እንዲያስጨብጥና የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን ለማጠንከር የተዘጋጀ ስልጠና ነው ፡፡