መረጃን ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ እምርታ ለመጠቀም የመረጃና ማስረጃ ሳይንሳዊ ኮንፍረንስ ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ4ኛ ጊዜ የሚከበረውን ሳይንሳዊ የመረጃና ማስረጃ ዲጂታል ሳምንተዊ የጥናት ኮንፍረንስ መሰረት በማድረግ ሚያዚያ 24/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በመረጃ የታገዘ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በሚል በመረጃና ማስረጃ ላይ መሰረት ያደረገ ሳይንሳዊ ኮንፍረንስ ተካሄደ፡፡
የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ በጤናው ዘርፍ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ በሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ እንዲሁም በዲጂታል በመታገዝ የዜጎችን ጤና ማሻሻል፣ የመረጃ ጥራትን ማስጠበቅ፣ የመረጃ ፍሰትን ተደራሽነት የበለጠ ለማሳለጥ እና ለዜጎች ጤና መሻሻል ጉለህ ሚና እንዲኖረው ማድረግ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለጤና መሻሻል በአግባቡ እንዲውል ለማድረግና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥን በተዋረድ እንዲጠናከር ለማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር አስናቀ ወርቁ የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ዳይሬክተር በኮንፍረንሱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ባደረጉት ንግግር ሳምንታዊ የጥናት ኮንፍረንሱን በተመለከተ ከፌዴራል እስከ ክልል በርካታ የጤና መረጃዎች እየተሰሩ መሆናቸወን፣ ለዲጂታላዜሽንና ለመረጃ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን እንዲሁም ችግር ፈቺ የሆኑ፣ ለውሳኔ ሰጪ አካላት የሚያገለግሉ እና የጤናውን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል የሚችሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች በበቂና በጥራት ለውሳኔ ሰጪ አካላት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሱድ መሐመድ በጤና ሚኒስቴር የሰትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ መረጃና እስታቲክስ ቡድን መሪ የኮንፍረንሱን ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለኮንፍረንሱ መሳካት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ አካላትና ለተሳተፉ ባለሙያዎች ምስጋና አቀርበዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊወክሉ የሚችሉና ከፍተኛ መሻሻል ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ የጤና መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ በመረጃ ትንተና እና ቅመራ ላይ ትኩረት ተደርገው የተሰሩ የተለያዩ ጥናታዊ ምርምሮች በጽሁፍና በባነር ገለጻ ቀርበው ውጤታቸውን አስመልክቶ በመድረኩ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የቀረቡት በርካታ ጥናቶቸ ሳይንሳዊ መረጃዎችና ማስረጃዎች ለጤናው ሴክተር ስትራቴጅክ ውሳኔ እና ፖሊሲ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑ ከነበረው የውይይት መድረከ ትኩረት በመስጠት ተብራርተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እና ጤና ላይ ሳይንሳዊ ምርምር የሚያደርጉ የዩኒቨርስቲ እና የኮሌጅ ተመራማሪ ባለሙያዎች እንዲሁም የአጋር ድርጅ ኃላፊዎች በጥናታዊ ኮንፍረንሱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡