በሀገራችን የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታ አስመልክቶ የተሰጠ ወቅታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ

በሀገራችን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ሕዳር 5 ቀን 2018 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲሁም የህብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ የጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ከክልል ጤና ቢሮዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ የሙያ ስብጥር ያካተተ ከፍተኛ ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን በማደራጀት በሽታዉን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የማህበረሰብአቀፍ የቅኝት ስራዎች፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማከም፣ ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ንክኪ ያላቸዉን ሰዎች የመለየት ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ እንዲሁም በክልል ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የክስተት አስተዳደር ስርዓት (Incident Management System)ተቋቁሞ የፈጣን ምላሽ ስራዎችን በማስተባበር ላይ ይገኛል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የመጀመሪያው የበሽታው ታማሚ ከተገኘበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ፡ እስከ ዛሬ ድረስ በበሽታው ለተጠረጠሩ ለ73 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 11 በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ተረጋግጧል፤ እነዚህ ታማሚዎች አስፈላጊው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የነበረ ቢሆንም የ6ቱ ህይወት ያለፈ ሲሆን የተቀሩት 5ቱ ደግሞ በህክምና ጣቢያ ወስጥ ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡
የበሽታው ምልክቶች ከታየባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው 349 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 119ኙ የክትትል ጊዜያቸውን ጨርሰው ከለይቶ ማቆያ እንዲወጡ ተደርጓል።
የላቦራቶሪ የመመርመር አቅምን ከማሳደግ አኳያ የቫይረሱን ዘረ መል ለመለየት የሚያስችል የላቦራቶሪ አቅም የገነባን ሲሆን ተንቀሳቃሽ የላቦራቶሪ መመርመሪያ እና ሌሎችም አስፈላጊ ግብአቶችን ወደክልሉ በመላክ የተሰበሰቡ ሁሉም ናሙናዎች ረጅም ርቀት ሳይጓጓዙ ባሉበት ቦታ ለመመርመር እንዲቻል ተደርጓል። የበሽታውን መነሻ ለማወቅም አሁንም ጥረቶች እና ምርመራዎች እየተደረጉ ሲሆን ውጤቱ ሲደርስ ለሕብረተሰባችን የምናሳውቅም ይሆናል።
ከዚህም በተጨማሪም ወረርሽኙ በተሰተባቸው አካባቢዎች የለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን በማቋቋምና የሰለጠነ የሰውሃይል እና አስፈላጊውን የህከምና ግብአት በማደራጀት ለታማሚዎች የተጠናከረ የህክምና እርዳታ እየተሰጠ ሲሆን ለታማሚዎችም የተሻለ ሕክምና ለመስጠት ይቻል ዘንድ ከዚህ በፊት ወረርሽኙ ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግና ልምድ በመቅሰም ከዚህ በፊት ተሞክረው ጥሩ ውጤት ያስገኙ መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በመለየትና ወደሃገር ውስጥ በማስገባት ለታካሚዎች ተደራሽ በማድረግ ላይ እንገኛለን።
ከዚህ በተጨማሪም በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ከነበራቸው የማህበረሰባችን አካላት ጋር በበሽታው የመያዝ እድላቸውን ለመቀነስ የሚያግዝ Remsedevir የተባለ የፀረ ህዋስ መድሃኒት ወደ ሃገራችን ውስጥ በማስገባት እስካሁን 16 ለሚሆኑ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ተብለው ለታሰቡ የህክምና ባለሙያዎችን እና ለታማሚዎች ለማድረስ ችለናል፡፡
በሽታው ባልተገኘባቸው የሀገራችን ክፍሎችም ወደፊት በሽታው ቢከሰት ሀከምና ለመስጠት የሚያስችሉ የለይቶ ማከሚያ እና ማቆያ ማዕከላት በሰለጠነ የሰው ሃይል፥ በግብዓትና በሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በሰፊው እየተሰሩ ይገኛሉ።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከሕብረተሰቡ ጋር ከምናደርገው የቅኝትና ልየታ ስራ በተጨማሪ በአገር በመውጫና መግቢያ ኬላዎች፥ በአየር ማረፊያዎች፥ እና ወረርሽኙ በተገኘባቸው አካባቢዎች የሚወጡና የሚገቡ ሰዎችን፣ ኬላዎችን በማቋቋም ሰፊ የልየታ ስራዎችን እየተሰሩ ይገኛል። በሚቀጥሉት ሳምንታት ከሚካሄደው ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ዘመቻ ጋርም በማስተሳሰር የቅኝትና የልየታ ተግባራት በሰፊው የሚከናወኑ ይሆናል።
የሕብረተሰባችን ግንዛቤ ከፍ እንዲል እና ወረርሽኙን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ማህበረሰባችን ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችሉ የሕብረተሰብ ጤና መልዕክቶችን ሁሉንም ሕብረተሰብ ተደራሽ ባደረገ መልኩ በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ መንገዶች በሰፊው እየተሰራጩ ሲሆን የብዙሀን መገናኛዎችም ሕብረተሰባችንን ከማስተማር አልፎ የበሽታው ምልክቶች የታየባቸውን ሰዎች የመለየትና ሪፖረት የማድረግ ስራዎች ላይም ትልቅ ሃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ።
አሁንም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ባለበት ለማስቆም ሕብረተሰባችን በንቃት ምክረ ሃሳቦችን እንዲከታተልና እንዲተገብር በአጽኖት ለማሳሰብ እንወዳለን።
● የበሽታውን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድና የጤና ምርመራ ማድረግ፣
● ለበሽታው ተጋላጭነት እንዳለ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ በሚጠየቁበት ጊዜ ፈቃደኛ በመሆን የራስን ጤና መጠበቅና በሽታውን ስርጭት መከላከል፣
● በሽታው ወደ ተገኘባቸው አካባቢዎች የሚደረግ ጉዞን መቀነስ፤
● ሁልጊዜ እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ወይም በሳኒታይዘር ማጽዳት፣
● ምልክት ከታየበት ማንኛዉም ሰዉ ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራስን የመከላከያ ዘዴዎች (እንደ ጓንት፤ የግል መከላከያ ቁሳቁሶች(PPE)) የመሳሰሉትን መጠቀም
● በበሽታው ተጠርጥረው ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን አስከሬን በሰለጠኑ ባለሙያዎች በጥንቃቄ የቅብር ስነ ስርዓት ማከናወን፣
● ወቅታዊ መረጃዎችንና የጥንቃቄ መልዕክቶችን ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መከታተልና መተግበር፣
የበሽታውን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰዉ በሚመለከቱበት ጊዜ በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ ወይም በ8335 እና 952 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ መስጠት የሚቻል ሲሆን፣ ስለበሽታው ተጨማሪ መረጃ እንዲሁም የምክር አገልግሎት ለማግኘትም እነዚህን የነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም ይቻላል።
በተጨማሪም አሁን ላይ በሁሉም የጤና ተቋሞቻችን መደበኛ የጤና አገልግሎቶች እና ክትትሎች እየተሰጡ በመሆኑ ማህበረሰባችን የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በጤና ተቋሞቻችን ማግኘት እንደሚችል መግለጽ እንፈልጋለን፡፡
የጤና ሚኒስትር
ሕዳር 17 ቀን 2018 ዓ/ም
ኢትዮጵያ