በምሥራቅ የሚገኙ የድንበር መውጫና መግቢያዎች ላይ ስለሚሰጠው የጤና ቁጥጥር አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንሲትቲዩት የተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት በምሰራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ የመግቢያና መውጫ ኬላዎችና የተጓዦች ጤና አገልግሎት በድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ በደዋሌ እና በቶጎጫሌ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እና ከነዚህ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ጋር የሪፈራል ትስስር ካላቸው ጤና ተቋማት እንዲሁም በድረዳዋና ጅግጅጋ ከተማ ለአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት አገልግሎት ከሚሰጡ የጤና ተቋማት ላይ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በድንበር ተሻጋሪ ተላላፊዎ በሽታዎች ቁጥጥር እና ለአለም አቀፍ መንገደኞች በሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ዙሪያ የጋራ የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ተመስጌን ለሚ የኢንሲትቲዩቱ የተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደ ተናገሩት በነዚህ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚሰሩ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጋራ መስራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
“ስለዚህ የዚህ የጋራ ውይይት ዋና አላማ በመግቢያና መውጫ ኬላዎች በሚሰሩ የድንበር ተሻጋሪ ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር እና በአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት አገልግሎት ዙርያ የሚሰሩ ስራዎች ላይ በጋራ በመወያየት በስራው ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ ዕቅድ በማውጣት በጋራ ለመስራት እድንችል የሚያስችለን ውይይት ነው፣” በማለት አቶ ተመስጌን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአራት አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ዘጠኝ የየብስ መግቢያና መውጫ (13 Designated Point of Entries) ላይ ኬላዎችን በማቋቋም መጠነ ሰፊ የሆኑ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ከመድረኩ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከነዚህም መካከል ድሬዳዋ አለም አቀፍ ኤርፖት፣ ደዋሌ እና ቶጎጫሌ የየብስ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ዋንኛዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡