በስትራቴጂካዊ የአደጋ ልየታና በባለብዙ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ መጠባበቂያ ዕቅድ ላይ ያተኮረ አዉደጥናት ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተጓዦችና እና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ለቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እና ለኩርሙክ መግቢያና መውጫ ኬላዎች የ ‘Strategic Risk Assessment and Developing Multi-hazard Public Health Emergency Contingency Plan (MHPHECP) for Bole International Airport and Kurmuk PoE ’ በሚል ርዕስ ከመጋቢት 1 እስከ 5/2017 ዓ.ም አውደጥናት አካሄደ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ የዚህ መሰል አዉደ ጥናት የተቋማቱን አቅም ለማጎልበትና ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ፋይዳዉ ብዙ መሆኑን በበይነመረብ ገልፀዉ የስራ መመሪያዎችን ሰጥተዋል።
የአዉደ ጥናቱ ዋና ዓላማም ለቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዲሁም ለኩርሙክ መግቢያ እና መውጫ ኬላዎችን በተመለከተ የአደጋ ልየታ (risk assessment) ስራዎች በማካሄድ ፤ በተለዩት አደጋዎች ዙርያም የቅድመ ዝግጅት እና የቁጥጥር ስራዎች እንዲሁም የተጠባባቂ እቅዶችን(contingency planning) ማዘጋጀት መሆኑን የክፍሉ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተመስገን ለሚ ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ የመግቢያና መውጫ ኬላዎች የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ዲቪዥን አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሸናፊ ሲሳይ አክለዉ እንደገለፁት ተጠባባቂ ፕላኑ(the MHPHECP) ከ 1-2 ዓመት ሊከሰቱ በሚችሉ አደጋዎች ዙሪያ ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ በሁሉም ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ከአዉደ ጥናቱ የሚገኘዉ የአደጋ ልየታዉ ዉጤት ክፍሉ በቀጣይ ለሚሰራው የ 5 አመት ስትራቴጂክ እቅድ እንደ ዋና ግብአት እንደሚጠቅም የተመላከተ ሲሆን አውደጥናቱ ከክፍሉ ጋር በቅርበት ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ፤ ከአጋር ድርጅቶች እና በተለያዩ አገራት ላይ ረዥም ዓመት የስራ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች እየታገዘ የሚሰራ በመሆኑ በቀጣይነት በሌሎች መግብያና መውጫ ኬላዎች ላይ ስራውን ለሚተገብሩ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ጥሩ የልምድ መለዋወጫ እና መማማሪያ መድረክ መፍጠሩ ተገልጿል።
በአውደጥናቱ ላይ በቦሌ እንዲሁም በኩርሙክ መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚሰሩ የተለያዩ የመንግስት እንዲሁም መንግስትታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ ተቋማት ተሳትፈዋል።