በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ወቅታዊ ምላሽ ሥራዎች አፈጻጸም ሳምንታዊው የውይይት ስብሰባ ተካሄደ
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በተገኙበት በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ህዳር 16/2017 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል በበይነ መረብ ሳምንታዊው የውይይት ስብሰባ ተካሄደ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ወቅታዊ የወባ ወረርሽኝን በተመለከተ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና ክላስተሮች ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶች እና ወረርሽኙ በአሁን ሰዓት ያለበትን ደረጃ ምን እንደሚመስል ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ የተለያዩ ስራዎች በተለይም የማሕበረሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ላይ፣ የቤት ለቤት ጉብኝት፣ የአጎበር ስርጭትና አጠቃቀም እንዲሁም አካባቢን የማጽዳት ስራዎች አፈጻጸም ውጤታማ መሆናቸውን፣ ለዚህም በሁሉም ክልሎች እና ክላስተር ወረዳዎች የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መሆኑን በቀጣይ ወራትም የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ሁሉ አቀፍ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራዎች ያለማቋረጥ በልዩ ትኩረት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተገልጿል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የውይይቱን ማጠቃለያ በሰጡበት በወቅት እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ ባለው ሁሉ አቀፍ የተቀናጀ ስራ የተሻለ ውጤት መመዘገቡን እና ወርሽኙም እየቀነሰ መምጣቱ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ በበቀጣይም ለበሽታው ስርጭት ምቹ ሁኔታዎችን መግታት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማድረግ የሕብረተሰቡን ተሳትፎና ግንዛቤ በማሳደግ የቅኝት ስራዎችን በጥራትና በብቃት በመፈጸም እንዲሁም ለውሳኔ በመጠቀም፣ መልካም እና ውጤታማ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራዎችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንድተገብር ማድረግ ኦንደሚገባ አሳስበዋል::
በተጨማሪም አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየት በጤና ኬላ ደረጃ እና በቀበሌ ደረጃ የሚሰሩ የመከላከልና የቁጥጥር ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየተሰሩ ያሉ በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን በሚገባ ተግባራዊ እየተደረጉ በመሆናቸው ወረርሽኙ እየቀነሰ እንዲመጣ ማስቻሉ ትልቅ ግብ መሆኑንና የወረርሽኙ መቀነስ ሳያዘናጋ አሁንም በየት/ቤት ለተማሪዎችን ስለ ወረርሽኙ እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ስራ እንዲሁም የማሕበረሰቡ ተሳትፎ የማሳደጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
አቶ ጉዲሳ አሰፋ በጤና ሚኒስቴር የወባ እና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ ከተለያዩ ክልሎችና ክላስተር ወረዳዎች ስለ ኬሚካል ርጭት፣ አጎበር ፣ መድሃኒት አቅርቦት እና ስለ ሌሎችም መሰል ጉዳዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡