በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የFrontline-FETP ሰልጣኝ የጤና ባለሙያዎች ተመረቁ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የወረዳ ጤና ተቋማት የተውጣጡና ለ3 ወራት መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Frontline-FETP) ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም በጅማ ከተማ ተመረቁ።

የምርቃት ፕሮግራሙን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ሲሆን ስልጠናው 3ኛ ዙር የጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የጤና ባለሙያዎችን የእውቀትና የክህሎት አቅም በማሳደግ፣ በሕብረተሰብ ጤና ላይ አደጋ የሚፈጥሩ የተለያዩ ወረርሽኞችንና ክስተቶችን ቀድሞ ለመለየት፣ መረጃዎችን በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ለማድረግ እና የምላሽ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ነው።
በምርቃት ስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨመሰ እንደገለጹት፤ ይህ ስልጠና በጤናው ዘርፍ ከሚሰጡ ሌሎች ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገው በተግባር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው:: ባለሙያዎቹ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም፣ በጥራት ላይ የተመሰረቱና ለውሳኔ ሰጪ አካላት መረጃዎችንና መፍትሔዎችን በማቅረብ የሕብረተሰቡን የጤና ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አወል ዳውድ በበኩላቸው፤ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በሙሉ አቅም ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ስልጠናውን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በተደረገው ከፍተኛ ጥረትም የመረጃ ወቅታዊነት፣ ጥራት እንዲሁም የምላሽ ስራዎች ላይ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ባለሙያ አቶ ጃፈር ከዛሊ እና የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ባለሙያ ወ/ሪት እናኑ ሁነኛው ተመራቂዎች ወደ ስራ ቦታቸው ሲመለሱ ስለሚኖራቸው ኃላፊነትና ተግባራት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ከሰልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰልጣኝ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው በስራ ቦታቸው የተሰጧቸውን የፊልድ ፕሮጀክቶች አጠናቀው በጽሁፍና በፊትለፊት ገለጻ (Presentation) አማካኝነት መገምገማቸውን ጠቅሰው፣ ስልጠናው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስመዝገብና ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን የዕለት ከዕለት የጤና አገልግሎቶች በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ስልጠናውን በብቃት ተከታትለው ያጠናቀቁና በአማካይ 70 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 28 የኮርሱ ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።