ተግባራዊ ሞሎኪውላር ኢፒዲሞሎጂን አስመልክቶ ለባለሙያዎች ስልጠና ሊሰጥ ነው

ተግባራዊ ሞሎኪውላር ኢፒዲሞሎጂን አስመልክቶ ለባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከኖርወይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተግባራዊ ሞሎኪውላር ኢፒዲሞሎጂ ለወረርሽኝ ቅኝትና ምርምር ስራዎች አስመልክቶ ለባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት የካቲት 25/2018 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል የዝግጅት አውደ ጥናት አካሄደ።
የስልጠናውን ዝግጅት አውደ ጥናት ዋና ዓላማ አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ማድረግና መነሻ ሐሳቦችን በመውሰድ የተግባራዊ ሞሎኪውላር ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ማንዋል ማዘጋጀት ነው።
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጅኖሚክስና ባዮኢንፎርማቲክስ ማዕከል በሀገር ደረጃ ትልልቅ የምርምርና የወረርሽኝ ቅኝት ምላሽ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአገሪቱ በአራት የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ላይ ይህ የጅኖሚክስ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከዚህ በፊት ወደ ውጭ አገር ይላኩ የነበሩ የተለያዩ የበሽታ ናሙናዎች በአሁኑ ወቅት በኢንስቲትዩቱ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የጂኖሚክስ የቅኝት ስርዓትን የበለጠ ለማጠናከርና የተሻለ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፣ በተለይም በፌዴራልና በክልል ደረጃ ያሉትን የበሽታ የቅኝት ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የጀኖሚክስ ዳታዎችን ለሕብረተሰብ ጤና ምላሽ መስጠት የሚቻልበትን የግንዛቤ ደረጃ ስለሚያሳድጉ እነዚህን መሰል ዝግጅቶች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አብርሃም አሊ በተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት የአርቦ ቫይረስ እና ሌሎች ቫይረስ ምርምር ዲቪዥን ኃላፊ አውደ ጥናቱን አስመልክቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ተግባራዊ የሞሎኪውላር ኢፒዲሚዮሎጂ በዘመናዊ የበሽታ ክትትልና ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ ውስጥ ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በዘረመል ተንተና የተገኙትን መረጃዎች ከኢፒዲሞሎጂ መረጃዎች ጋር በማቀናጀት ተላላፊ በሽታዎችን የመለየት የመቆጣጠር እና የመከላከል አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ መሆኑን፣ በተለያም የባለሙያዎችን አቅም በስልጠናዎች መገንባትና ማሳደግ እጅግ ወሳኝና አስፈላጊነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች የስልጠናውን አስፈላጊነት በመረዳት ለስልጠናው ዝግጅት ግብአት የሚሆኑ የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳት ውይይት አድርገዋል።