ተጨማሪ የጸረ ተዋህሲያን መድሐኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ ቅኝት ጣቢዎች በይፋ ስራ ጀመሩ

ዓለም አቀፉን የጸረ ተዋህሲያን መድሐኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ ቀንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከህዳር 11 – 12/2018 ዓ.ም በዚህ ረገድ እስካሁን የተሰሩ የቅኝት ስራዎችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመምከር በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ተጨማሪ የጸረ ተዋህሲያን መድሐኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ (#AMR) የቅኝት ጣቢዎች ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ዶ/ር ገመቹ ታደሰ በኢንስቲትዩቱ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መድረኩን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት AMR አሳሳቢ ከሚባሉት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አንዱ እና ዋነኛው እንደመሆኑ በቀጣይነት የሚሰሩ በርካታ ስራዎች ሲኖሩ ለዚህም ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ዛሬ በይፋ ስራ የጀመሩት አዳዲስ የAMR የቅኝት ጣቢዎች የሚጠቀሱ ሲሆን በዚህ ውይይትም የቅኝት ስርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት እናም አጠቃላይ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው ብለዋል። አያይዘውም የነዚህ ቅኝት ጣቢዎች መከፈት የመረጃ ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ያሉትን ግብዓቶች በብቃት ስራ ላይ ለማዋል እንዲሁም ያለውን የሰው ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱን ባለሙያዎች ጨምሮ ከጤና ሚኒስቴር፣ የተለያዩ የሆስፒታሎች አመራሮች እና የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩ ብሔራዊ የAMR ቁጥጥር እና መከላከል ከአንድ ጤና አንጻር፣ የAMR የቅኝት ግኝቶች ሪፖርት፣ የAMR ዝግጁነት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት እናም ሌሎች ተያያዥ ዶክመንቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

እስካሁን ከ16 የቅኝት ጣቢያዎች 87.987 ናሙናዎች ለAMR ክትትል መሰብሰባቸውን ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል።