አራተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በሀዋሳ ተጀመረ

አራተኛው ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ በየነ በራሳ፣ የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በሲዳማ ክልል ርዕሰ ከተማ ሀዋሳ ታህሳስ 03/2018 ዓ.ም ተካሄደ። ክትባቱ ከታህሳስ 3 – 6/2018 ዓ.ም ድረስ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ይሆናል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመርU ግብሩ ላይ እንደገለጹት የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ለዚህም ከፍተኛ በጀት ተበጅቶለት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል። በሀገራችንም ፖሊዮን ጨምሮ ከ15 በላይ ክትባቶችን በመደበኛነት በመከተብ የማህበረሰባችን የጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑንና የፖሊዮ በሽታ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ ለሀገር ብሎም ለአለም ትልቅ ጫናን የሚፈጥር በሽታ በመሆኑ በ2017 በጀት አመት በሁለት ዙር የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በ10 ክልሎች 15 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዕድሜያቸው ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ መደረጉን ክብርት ሚኒስተሯ ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ጤና ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊና ምርታማነትን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግና ጤነኛ ትውልድ በመገንባት ክልላዊ ራዕይን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በዚህ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻም በክልሉ ሁሉም ህጻናት እንዲከተቡ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ሀገራችንን ከተለያዩ የጤና አደጋዎች ለመከላከል በርካታ ስራዎች መስራቱንና አየሰራም እንደሚገኝ አስታውሰው ዋይልድ የሚባለውን የፖሊዮ ዓይነት ከሀገራችን ማጥፋት መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን እና አለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠውን የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለ24.5 ሚሊዮን ዕድሚያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአህጉራችን ካሉ ሀገራት ጋር በተደረገ የተቀናጀ እና ቁርጠኛ ርብርብ የዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ በሽታ በአፍሪካ አህጉርም ጭምር በመጥፋቱ በ2020 እ.ኤ.አ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ከ2019 እ.ኤ.አ ጀምሮ በኢትዯጵያ የተለያዩ አከባቢዎች በክትባት እጥረት የሚመጣ የፖሊዮ ወረርሸኝ እየተከሰተ ይገኛል። በአጠቃላይ በ2019 እ.ኤ.አ ጀምሮ 152 በክትባት እጥረት የሚመጣ የፖሊዮ ተጠቂዎች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን ባለፉት 12 ወራት ብቻ በላብራቶሪ የተረጋገጡ የፖሊዮ ተጠቂዎች ሪፖርት መደረጋቸውን የኢትዯጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ ገልጸዋል።
በዚህ የክትባት ዘመቻ ክትባት ያልጀመሩ ህፃናትን ማስጀመር፣ ክትባት ያቋረጡ ህፃናትን ማስቀጠል፣ ቆልማማ እግር ያላቸው ህፃናት ልየታ፣ ቤት ውስጥ ለረዥም ጊዜ በህመም አልጋ ላይ ያሉ ዜጎችን መለየት እና በማርበርግ ቫይረስ በሽታ የተጠረጠሩና ምልክት የሚያሳዩ አካላትን ለይቶ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ ተቀናጅተው የሚሰሩ ተግባራት መሆናቸውን ያመላከቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ሲሆኑ በክልሉ አንድ ሚሊዮን አርባ ዘጠኝ ያህል ህጻናት እንደሚከተቡ የገለጹት ደግሞ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ ናቸው። የአለም ጤና ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ኦስሎ እና የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሀዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ክቡር አጋና ኔቶም በመርሀ ግብሩ ላይ የየበኩላቸውን ቁልፍ መልዕክቶች አስተላልፈዋል።