ኢንስቲትዩቱ ለአቅመደካማ ቤተሰብ ያደሰውን ቤት ርክክብ አደረገ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ም/ዋና ዳይሬክተሮች በተገኙበት በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 አስተዳደር በብሎክ አራት አካባቢ የሚገኙ የአንድ አቅመደካማ ቤተሰብ ሙሉ ቤት እድሳት በማድረግና በማጠናቀቅ ታህሳስ 25/2017 ዓ.ም ቤቱ ለታደሰላቸው አቅመደካማ ርክክብ አደረገ፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ አንጋፋ ከሚባሉ ረጅም ዘመናትን ተሻግረው አሁን ላይ ሕዝብን እያገለገሉ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ መሆኑን፣ የሕብረተሰብ ጤናን ከማስጠበቅ አንጻር በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ እንዲሁም ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ ሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ በሕብረተሰቡና በመንግስት የሚሰጡትን ተልዕኮዎች መሰረት በሚገባ እየተወጣ ያለ ተቋም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ አቅመደካማ የሆኑ ሰዎችን በማገዝ፣ ህጻናትን በማስተማር፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለጤና ተቋማት የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመደገፍ በኩል ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር በመተባበር ከፍተኛ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሶስት ቤቶችን ለአቅመ ደካማ ሰዎች ሁለቱን በአዲስ አበባ ከተማ አንዱን ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ በማደስና በማጠናቀቅ ኢንስቲትዩቱ ማስረከቡንና በአራተኛ ደረጃ አሁን ተገኝተን ርክክብ እያደረግን ያለውን ቤት ለእነዚህ አቅመ ደካማ ቤተሰብ ኢንስቲትዩቱ በማደስና በማጠናቀቅ ማስረከብ በመቻሉ በተቋሙ ስም ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቤቱ የታደሰላቸው ቤተሰብም የቤቱን ቁልፍ በመረከብ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ላደረገላቸው ድጋፍም ልባዊ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡