ኢንስቲትዩቱ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ስለሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንሲቲትዩት የተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ከጅቡቲ ጋር ከሚዋሰኑ ጋላፊ እና ሌይ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እና በክልሉ ከሚገኘው የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የአለም አቀፍ መንገደኞች ክትባት ማዕከል ላይ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በድንበር ተሻጋሪ ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር እና ለአለም አቀፍ መንገደኞች በሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ዙሪያ ከታህሳስ 5-6/2017 ዓ.ም የጋራ የውይይት መድረክ በሰመራ ከተማ አካሄደ፡፡
አቶ ተመስጌን ለሚ የኢንሲትቲዩቱ የተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደ ተናገሩት በነዚህ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እና የአለም አቀፍ መንገደኞች ክትባት ማዕከል ላይ የሚሰሩ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ስራዎች እና ለአለም አቀፍ መንገደኞች የሚሰጠውን የክትባት አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጋራ መስራት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ስለዚህ የዚህ የጋራ ውይይት ዋና አላማ በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በሚሰሩ የድንበር ተሻጋሪ ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር እና በአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት አገልግሎት ዙርያ ኢንስቲትዩቱ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ከጅቡቲ ጋር ከሚዋሰኑ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እና በክልሉ በሚገኙ የአለም አቀፍ መንገደኞች ክትባት ማዕከላት በሚሰሩ ስራዎች ላይ በጋራ በመወያየት በስራው ሂደት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የጋራ ዕቅድ ማውጣት እና ችግሮቹንም ለመፊታት በቅንጅት ለመስራት የሚያስችለን የውይይት መድረክ ነው፣” በማለት አቶ ተመስጌን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ተያያዥ የሆኑ ሪፖርቶች ቀርበው ወይይት ተደርጐባቸው ተሳታፊዎች በቡድን ቡድን በመሆን መሰራት ስላለባቸው ተግባራት በዝርዝር የተግባር ዕቅድ አስቀምጠዋል።
አቶ አብዱ አሊ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ኃላፊ እነዚህ ኬላዎች ወደ ሀገር ወሳኝ መግቢያና መውጫ በመሆናቸው አሁን ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ካሉ ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የመድረኩ አስተባባሪዎች እንዳስታወቁት ከቀሩት የሀገር መውጫ እና መግቢያ ኬላዎችም ጋር በቅርቡ ተመሳሳይ መድረኮች ይኖራሉ።
በአሁኑ ወቅት በመላው አገርቷ አራት አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ዘጠኝ የየብስ መግቢያና መውጫዎች በአጠቅላይ በ13 Designated Points of Entry ላይ ኬላዎችን በማቋቋም መጠነ ሰፊ የሆኑ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን እንድሁም 13 የአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት ማዕከላት (5 በቅርብ በተቋቋሙት) ላይ ለአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት አገልግሎት የመስጠት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ከመድረኩ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከነዚህም መካከል ጋላፊ እና ሌይ የየብስ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እና ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የአለም አቀፍ መንገደኞች የክትባት ማዕከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡