ኢንስቲትዩቱ በአካቶ ትግበራ አፈጻጸም 1ኛ በመሆን ተሸለመ

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጤና ሚኒስቴር እና በግብርና ሚኒስቴር ስር የሚገኙትን 22 ተጠሪ ተቋማት የሴቶች፣ህፃናት ፣ወጣቶች፣አካል ጉዳተኞች፣አረጋውያን እና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጉዳዮች አካቶ ከመሰራትና የአካቶ ትግበራ ስርዓት ከመዘርጋት አንፃር በተደረገ ምዘና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ 1ኛ ደረጃ በመዉጣት ተሸልሟል።
የዕውቅና መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሌሎች ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም ግን በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የአካቶ ትግበራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቶች፣ ምልከታዎችና የዳሰሳ ጥናቶች የሚፈለገውን ያክል አለመድረሱን ማመላከታቸውን ጠቁመዋል።
የኢንስቲትዩቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሮም ሞረዳ እንደተናገሩት የእነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ ተቋማዊ በማድረግ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በኢንስቲትዩቱ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን አሁን የተሰጠው የዕውቅናም ለስራው የበለጠ መሳለጥ የሚያበረታታ ነው።
የእውቅና ሽልማቱን ወ/ሮ የሮም ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ጋር በመሆን ተቀብለዋል።