ኢንስቲትዩቱ ከሚዲያ አካላት ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚዲያ አካላት ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አካሄደ::የሲዳማ ክልላዊ መንግስት የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘመናዊ ላብራቶሪም በሚዲያ ባለሙያዎች ተጎብኝቷል::

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ከሀገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ልየታ፣ ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ፣ በአንድ ጤና (One Health) ትግበራ፣ በዓለም አቀፍ የጤና ደንብ (IHR)፣ በሕብረተሰብ ጤና ጥናትና ምርምር፣ በላብራቶሪ አቅም ግንባታ እና በጤና መረጃ አስተዳደር ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል። በተጨማሪም በተቋሙ አጠቃላይ የመቶ ዓመታት ታሪካዊ ጉዞ፣ የወቅቱ የስራ እንቅስቃሴዎችና ዋና ዋና ተግባራት ላይ ሰፊ ማብራሪያ ቀርቧል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት መቶ ዓመታት በምርምር፣ በበሽታዎች ቁጥጥርና በላብራቶሪ አገልግሎት የሕብረተሰብ ጤና ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ የልህቀት ማዕከል መሆኑን አብራርተዋል።
ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ የመለየት፣ የምላሽ አሰጣጥ አቅምን የማሳደግ፣ በማስረጃ ላይ የተደገፉ የፖሊሲ ግብዓቶችን በምርምር የማቅረብ እና የላብራቶሪዎችን አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገንባት ስራዎችን በዋናነት እያከናወነ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ዶ/ር መሳይ አክለውም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ወረርሽኝ ሲከሰት ማህበረሰቡን በወቅቱ ለማስገንዘብ እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የሰዎችን፣ የእንስሳትንና የአካባቢን ጤና በጋራ የሚመለከተውን የ”አንድ ጤና” (One Health) ፕሮግራምን እንዲሁም የዓለም አቀፍ የጤና ደንብን (IHR) መስፈርቶች በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከመጠቀም፣ የምርምር ስራዎችን ከመደገፍና የላብራቶሪ አቅምን ከፍ ከማድረግ እንዲህም ስራዎችን ዲጅታላይዝ ከማድረክ አኳያ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። የሚዲያ ባለሙያዎችም ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት በመስራት እና በመጎብኘት መረጃ በማስራጨት አብረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል::
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው፣ የሕብረተሰቡን ጤንነት ለማጎልበት የሚሰሩ የምርምር ውጤቶችን ይፋ ለማድረግ፣ ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚዲያ ሚና የማይተካ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በሕብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና ጠቃሚ ሐሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችም ከተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። ይህ የምክክር መድረክ በኢንስቲትዩቱ እና በሚዲያ ተቋማት መካከል ያለውን የስራ ግንኙነት ይበልጥ ዘላቂ፣ ስልታዊና የተቀናጀ ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የተሳታፊ ጋዜጠኞች ቡድንም የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘመናዊ የላብራቶሪ መሠረተ ልማትንና የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝቷል።