ኢንስቲትዩቱ የጋራ ክትባት ፕሮግራምና በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ላይ የጋራ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ክትባት ፕሮግራምና በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ላይ ያተኮረ የጋራ አፈፃፀም ግምገማ በቢሾፍቱ እያካሄደ ይገኛል።
በዚህ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ክትባት በኢትዮጵያ የጤና ፕሮግራም ላለፉት አራት አስርት አመታት ሰፋፊ ስራ የተሰራበትና የህፃናትን ሞት መቀነስ የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ ሰባት አይነት ክትባቶች እየተሰጡ እንደሚገኙም ጠቁመው፤ በቅርቡ አዳዲስ ክትባቶችን ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቅርቡም ከ7 ሚሊዮን በላይ ልጅ አገረዶችን የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት መከተብ መቻሉን ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም የጉበት፣የኩፍኝ፣ ወባና ሌሎች ክትባቶችን በተመረጡ ወረዳዎች ላይ በማስጀመር ጥረቱ እንደሚጠናከር ጠቁመዋል። ይህ በመደረጉ ባለፉት አመታት ከአምስት አመት በታች የሚከሰተውን የህፃናት ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ክትባት በሽታዎችን ከመከላከልና ሞትን ከመቀነስ አኳያ ውጤታማ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህ አንፃር የክትባት ፕሮግራሞቹ የበሽታ መከላከልና የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥሩን ስራ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተቋሙ አደረጃጀት በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች ቅኝት ስራዎች በተጨማሪ የምርም ዲቪዚዮን በመናበብ የፕሮግራም ስራዎች ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። እነዚህን ስራዎች ከክልልሎች ጋር የማናበብ ስራ በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል። የፖሊዮ ወረርሽኝ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ሲከሰት የተለያዩ የምላሽ፣ ቅኝት፣ ልየታና የክትባት ስራዎችን ኢንስቲትዩቱ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው በቅንጅት ስንሰራ ውጤት አስመዝግበናል ያሉ ሲሆን ለምናመጣቸው ውጤቶች በቅንጅት መስራታችን መሰረቶቻችን ናቸው ብለዋል። በክትባት ዘመቻዎቻችን ከሰራናቸው የፕሮግራም ስራዎች በየደረጃው እስከታች ድረስ መስራታችን ውጤት አምጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ አንፃር ከላይ እስከታች ድረስ አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የቅንጅት ስራው ስረአትን በተከተለ መልኩ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ እስከታች ድረስ እንዲቀጥል ባህል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ስራ አሰፈፃሚ ዶ/ር ማራማዊት አስፋው የክትባት ስራ ውጤታማ የሚሆነው ተቀናጅቶ መስራት ሲቻል መሆኑን ገልፀው፤ ከላይኛው እስከታችኛው አመራር ድረስ ቅንጅታዊ ስራ በመኖሩ በርካታ ለውጦች መምጣተቸውን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ተስፋዬ ክበበው ባለፉት አመታት በክልሉ በርካታ ክትባቶች ሲሰጡና ሩቲን ኢሚዩናይዜሽንን የማጠናከር ብሎም ወረርሽኞች ሲነሱ የዘመቻ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን በተለየ ሁኔታ በክትባት ላይ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጀምሮ ቅንጅታዊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚሁ የቅንጅት ስራ ጥሩ ውጤት መገኘቱንና ይህ ስራ እንዴት መቀጠል እንዳለበትና አብሮ መስራት ምን ያህል ጥቅም እንደሚያስገኝ የታየበት በመሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊዎች፣ የጤና ሚኒስትር ተወካዮችና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አመራሮች እና አጋር ድርጅቶች እየተሳተፋ ይገኛሉ።