ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቫይራል ሎድ (VL) እና የጨቅላ ህጻናት የኤች አይ ቪ ምርመራ (EID) ግምገማ …

ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቫይራል ሎድ (VL) እና የጨቅላ ህጻናት የኤች አይ ቪ ምርመራ (EID) ፕሮግራሞች የ2018 ዓ.ም. አገር አቀፍ የአፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከCU-ICAP ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የ2018 ዓ.ም. አገር አቀፍ የኤች አይ ቪ ቫይራል ሎድ (HIV Viral Load/VL testing) እና የጨቅላ ህጻናት የኤች አይ ቪ ምርመራ (Early Infant Diagnosis/EID) የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ከሰኔ 22-24/ 2018 ዓ.ም አካሂዷል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች/የክልል ሪፈራል ላቦራቶሪዎች፣ የናሙና ማጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ ተቋም፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ በበጀት ዓመቱ በዚህ ዘርፍ የተገኙ አበረታች ውጤቶች እና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መፍታት ያለባቸውን ተግዳሮቶች የዳሰሱ ሲሆን፣ አያይዘውም የኤች አይ ቪ ቫይራል ሎድ እና የጨቅላ ህጻናት የኤች አይ ቪ ምርመራ አገልግሎቶች የኤች አይ ቪ ህክምናን ውጤታማ ለማድረግ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና ውሳኔ ለመስጠት ያላቸውን ወሳኝ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም ይህንን እና ሌሎች የጤና የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን ጥራት፣ ተደራሽነትና ቀጣይነት ለማሻሻል የሰው ኃይል አቅምን፣ መሣሪያዎችንና ግብዓቶችን ለማጠናከር ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህ አውደ-ጥናት በዋናነት የተዘጋጀበትን ዓላማ እና ከዚህ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማ የሚገኙ ግኝቶችን በተግባር በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ሁሉም አካላት በትብብርና በባለቤትነት እንዲሰሩ አሳስበዋል። በበጀት ዓመቱ ለተገኙ ቁልፍ ውጤቶችም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አመስግነዋል።
በአውደ-ጥናቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልሎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት አፈጻጸም በጽሑፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዋናነትም በክፍተት የተገመገሙ እና መሻሻል ያለባቸው ሥራዎች ተለይተው የማሻሻያ ዕቅድ በማውጣት አውደ-ጥናቱ ተጠናቋል።