ዘርፈ ብዙ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ ዓውደ-ጥናት ተካሄደ

ዘርፈ ብዙ የላቦራቶሪ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ ቴክኒካል ኮሚቴ (Multi-Sectoral Biosafety and Biosecurity Technical Committee) የተቋቋመ ሲሆን፤ በሀገር ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኘው የላቦራቶሪ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ መርሃ-ግብር ዓውደጥናት በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡
የቴክኒካል ኮሚቴ አባላት የሆኑት ተቋማትና ሴክተሮች ማለትም ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት፣ የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ መከላከያ ሚኒስቴር ፣የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዓውደ ጥናቱ የተሳተፉ ሲሆን፤ በዓውደ-ጥናቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ መልዕክት የባዮሴፍቴ እና ባዮሴኪዩሪቲን ሥርዓት ትግበራ ከማሻሻል አንጻር አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመስራት የጤና ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ የባዮሴፍቲና ባዮሴኪዩሪቲ መስፈርቶችን እና ስታንዳርዶችን አሟልተው እውቅና እዲያገኙ አዲስ የእውቅና መርሀ ግብር ሥርዓት በመቅረጽ በሀገር ደረጃ ተገባራዊ ማድረግ ጀምሯል፤ በዚህ መርሀ ግብርም 16 ተቋማት እወቅና አግኝተዋል፤ በርካታ ተቋማት በእወቅና መርሀ ግብሩ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፤ አበረታች ውጤቶችም ተገኝተዋል በማለት ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው አያይዘውም የባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ ሥርዓት ከማጠናከር አንፃር በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው የአደገኛ ተህዋሲያንና መርዛማ ንጥረ ነገሮች ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴው ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በርካታ ተግባራት እንደሚጠበቅበት እና የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ የጤና ደንብና የአንድ ጤና (IHR and One Health) ጽ/ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ፈይሣ ረጋሣ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገር እና በዓለም አቀፍ የሚከሰቱትን ወረርሽኞች ከመከላከል አንፃር የላቦራቶሪ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ ፕሮግራም ማጠናከርና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ር ኢዮብ አበራ ለዓውደ ጥናቱ የውይይት መነሻ ሀሳብ እና የኮሚቴው መተዳደርያ ደንብን በጽሁፍ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት የተካሄደበት ሲሆን እንዲሁም በጤና እና በግብርና ዘርፍ በላቦራቶሪ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ መርሃ-ግብር የተከናወኑት ተግባራት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በተጨማሪም በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የላቦራቶሪ ባዮሴፍቲ እና ባዮሴኪዩሪቲ Advocacy and Communication ስትራቴጂ ስነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበት ከተሳታፊዎች ግብረ-መልስ እና ግብዓት ተሰጥቶበት እንዲካተት ተደርጓል፡፡