የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ግብዓቶች አቅርቦት ሰንሰለትን ለማጠናከር ሀገር አቀፍ ዕቅድ በመዘጋጀት ላይ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዩኤስ አስፐር (US ASPR)፣ ከአሜሪካው የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል (US CDC) እና ከግሎባል ዋን ሄልዝ ጋር በመተባበር በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ወቅት አስፈላጊዎቹን የቁጥጥር አቅርቦቶችን በወቅቱና በተቀናጀ መልኩ ለማድረስ የሚያስችል ብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች አቅርቦት ሰንሰለት ዕቅድ (National PHE MCM Plan) እያዘጋጀ ነው።

ዕቅዱ በአደጋ ጊዜ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች አቅርቦት በትክክለኛው ጊዜ፣ በተገቢው መጠንና በሚያስፈልገው ቦታ እንዲደርሱ የሚያስችል የተቀናጀ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ነው።
በዕቅድ ዝግጅት አዉዳ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች መኖራቸው ብቻ የሚሰጠውን ምላሽ ውጤታማ አያደርጉትም። የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች አቅርቦት በተገቢው ሁኔታ መለየት፣ ማሰራጨት፣ በአግባቡ አገልግሎት ላይ ኢንድዉልና የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ መደረጉ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር መልካሙ፣ ኢንስቲትዩቱ በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ የልህቀት ማዕከል ለመሆን በሚያደርገው ጥረት፣ የበሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች አቅርቦትና የሎጂስቲክስ አስተዳደርን ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ጠቁመው፣ ከማዕከላዊ የአቅርቦት ሥርዓት እስከ ክልሎች፣ የጤና ተቋማትና ታችኛው የማሕበረሰብ ክፍል ድረስ ያለውን የማከማቻ፣ የማሰራጨትና ምላሽ መስጫ ቦታ ድረስ (Last mile) የማድረስ ሂደት በተቀናጀ መልኩ ማስተዳደር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢንስቲትዩቱ የበሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ በበኩላቸው፣ ዕቅዱ በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ ሁኔታዎች ወቅት ሕይወት አድን የሆኑ ግብዓቶች አቅርቦት በተፈለገው ጊዜና ቦታ እንዲደርሱ በማስቻል የሀገሪቱን የአደጋ ምላሽ አቅም እንደሚያጠናክር ገልጸው ዕቅዱ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ፣ የግብዓት ፍላጎትን በቅድሚያ መተንበይ ከማስቻሉም በላይ የክምችትና የስርጭት ሥርዓቶች እንዲጠናከሩ ጠንካራ መሠረት እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።
በአሜሪካው አስፐር ስር ያለው የስትራቴጂክ ናሽናል ስቶክፓይል (SNS) ከፍተኛ አማካሪ ማይክል አየርስ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት በማውሳት፣ በተቀናጀ መልኩ መሥራት በአደጋ ጊዜ አስፈላጊ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች በፍጥነት ለሚያስፈልጋቸው ሕብረተሰቦች እንዲደርሱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያለውን ቀጣይ ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
በአዉደ ጥናቱ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ከመነሻ እስከ መድረሻ ያሉ የባለድርሻ አካላት ሚናና ኃላፊነትን መለየት፣ ማከማቸት፣ ማሰራጨት እና ከመነሻ እስከ መድረሻ ድረስ ያሉ ሂደቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መለየት፣ የአደጋ ምላሽ የቅንጅት ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የዝግጁነትና የምላሽ ዕቅድ ማዘጋጀት ላይ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ዕቅዱ ተግባራዊ ሲሆን፣ በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ወቅት የድንገተኛ አደጋ ግብዓቶች አቅርቦቶች በፍጥነት፣ በተቀናጀና በውጤታማ ሁኔታ እንዲደርሱ በማስቻል የኢትዮጵያን የሕብረተሰብ ጤና ደህንነትና የአደጋ ምላሽ አቅምን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።