የማርበርግ ቫይረስ በሸታ ወረርሽኝን ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንዲቻል ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው ለጤና ባለሙያዎች፣ ለአመራርና ለባለድርሻ አካላት ምስጋና ለማቅረብ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በእስካይላይት ሆቴል የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን በአጭር ጊዜ በመቆጣጠር በሕብረተሰቡ ብሎም በአገር ላይ ሊደርስ ከሚችለው ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ ጉዳቶች መታደግ የተቻለው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትብብር ከላይ እስከታች በሚገባ ተናቦ መስራት በመቻሉ ፤ እንዲሁም በጤና ባለሙያው በኩል ከራስ በላይ ለዜጐች በማሰብ መስዋዕትነት መክፈላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም የተዘጋጀው ፕሮግራም የአገር ባለውለታ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን ለማመስገን መሆኑን ጠቁመው በተቋም መረጃ የሕብረተሰቡን ጤና በማስጠበቅ በኩል ለመቶ ዓመታት ከፍተኛውን ኃላፊነት ሲወጣ የቆየና አሁንም ከመቶ በላይ ምርምሮችን ያካሄደ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የላቡራቶሪ አቅም የገነባ፣ የሕብረተሰብን ጤና በማስጠበቅ በኩል በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን አላማውን እያሣካ የሚገኝ ትልቁ አለኝታችን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኝን የመቆጣጠር አቅም መፈጠሩን፣ ለዚህም ከላይ እስከታች የሚናበብና በቅንጅት የሚሰራ፣ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የጤና ስርዓት መገንባቱንና በዚህ የጤና ስርዓት በመጠቀም የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢንስቲትዩቱ እና ከአጋር አካላት የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች ግብረ ሐይል በመቋቋም ከሕብረተሰቡ ጋር በመናበብና በቅንጅት ርብርብ በማድረግ ሶስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የማርበርግን ቫይረስ ወረርሽኝን መቆጠጠር በመቻሉንና ለዚህም ዋጋ ለከፈሉ የጤና ባለሙያዎች የምስጋና እውቅና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የማርበርግ ወረርሽኝን የመቆጣጠር እና የምላሽ የመስጠት ስራ ወቅት የታዩ አጠቃላይ ጠንካራ ጎኖችን አስመልክቶ እንዲሁም በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ከፍተኛውን ድርሻ ለተወጡ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ብሎም አጋር አካላት የእውቅና ሽልማትና የሰርተፍኬት ስነ-ስርዓት ተካሂዶ የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡