የምስራቅ ኢትዮጵያ የIHR አቅም ግምገማ

የሐረሪ እና የሶማሊ ክልሎችን እና የድሬዳዋ መስተዳድርን፣ የአለማቀፍ የጤና ህጎች (International Health Regulations/IHR/) ለመትግበር የሚያስችሉ መሠረታዊ አቅሞችን ሁኔታ ለመገምገምና የአቅም ግንባታ ዕቅዶችን ለማዘጋጀት ያለመ አውደ ጥናት በድሬዳዋ በመካሄድ ላይ ነው።

የኢትዯጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ወይይቱን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና ደህንነት ዙሪያ የህብተሰብ ጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ከማዘመን ጀምሮ አዳዲስ የህብረተሰብ ጤና ችግሮችን በሚገባ በመረዳት ቀድሞ በመለየት እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት እና የመልሶ ማገገም እንዲሁም ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በድንበር መውጫ እና መግቢያ ኬላዎች ላይ ጠንካራ የቅኝትና ቁጥጥር እና ሌሎች የመረጃ ስርዓቶችን በመዘርጋት ዜጎች ንቃተ ጤና እንዲጨምር ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚህም አጅግ አመርቂ የስኬት ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለዚህም ከክልሎች አስከ ወረዳዎች ድረስ የዘረጋናቸው ስርዓቶች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ዶ/ር መሳይ አያይዘውም አሁን ለምስራቁ የሀገራችን ክልሎች እና መስተዳድር የሚዘጋጀው በዋነኝነት የሚለየው እነዚህ ቦታዎች ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምንገናኝባቸው ኮሪደሮች እንደመሆናቸው ኢንስቲትዩቱም የድንበር ጤና ቁጥጥር በሰፊው የሚሰራባቸው ክልሎች በመሆናቸውና ከውጭ ተጓዦች ጋር ማህበረሰባች ጋር ሰፊ መስተጋብሮች ስላሉ ይህንና የአከባቢውን ማህበረሰብ አኗኗር ያገናዘበ እቅድ ሊዘጋጅ ይገባዋል በማለት ጠቅሰዋል።
ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ የድሬዳዋ መስተዳድር የጤና ቢሮ ሃላፊ በአውደ ጥናቱ በዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች በጥልቀት ምክክር እንደሚካሄድ፣ በአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለሚቀጥለው የጤና አደጋ ምን ያህል ተዘጋጅተናል? ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን፣ የላቦራቶሪ አቅማችንን እንፈትሻለን ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ሃይል ልማት ላይ እናተኩራለን በማለት ተናግረዋል።
የሶማሊ ክልል የጤና አማካሪ በበኩላቸው ይህ ውይይት የሀገራችንን ብሎም የክልሎቻችንን የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመለየት፣ የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅማችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን ሁሉንም ሴክተሮች በማቀናጀት ወደ አንድ የሚያመጣ ተግባራዊና የተቀናጀ አቅድ እንደሚዘጋጅ እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የአንድ ጤና /One Heath/ እና የአለም ዓቀፍ የጤና ደንብ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ በበኩላቸው የውይይቱ ዋና ዓላማዎች የአለማቀፍ የጤና ህጎች ለመትግበር በክልል ደረጃ ያሉ መሠረታዊ አቅሞችን ሁኔታ መገምገምና የአቅም ግንባታ ዕቅዶችን ማዘጋጀት መሆናቸውን ገልጸው ከውይይቱም በክልል ደረጃ አሁን ያለውን የጤና ደህንነት አቅምና ግንኙነት ማጠናከር፣ በአለም የጤና ደንቦች አፈፃፀም ላይ ያሉ ክፍተቶችን መለየት፣ የክልል መንግሥታትን ቁርጠኝነት መጨመር እና በ“አንድ ጤና” ዘርፎች መካከል ግንኙነትና ትብብር መጠናከር መሆኑን ገልጸው ተመሳሳይ መድረክም ከአማራና አፋር ክልሎች ጋር የተካሄደ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥም ሁሉንም ክልሎች ለማዳረስ መታቀዱን አስረድተዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዩኬ የጤና ደህንነት (UK Health Security Agency)፣ የሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይፍ እንዲሁም የኮር ግሩፕ እና የHOPE ተወካዮች ለዚሁ አላማ ሁሌም በተለያየ መልኩ ሲደግፉ የነበሩ እናም እየደገፉ እንዳሉ እናም ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።