የተቀናጀ ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዓለም የፖሊዮ ቀንን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ፖሊዮን ዜሮ የማድረግ ጉዞ በሚል መሪ ቃል ከሕዳር 27/2017 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት የሚሰጠውን የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በጋምቤላ ከተማ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በአማራ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ ክልሎች፣ በአበባ ከተማ መስተዳድር፣ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ መስተዳድር ክትባቱ የሚሰጥ ሲሆን በሶማሌ ክልል በሊበንና ዳዋ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ መስተዳድር፣ በቦረና እና በምስራቅ ቦረና ዞኖች የመጀመሪያ ዙር ፖሊዮ ክትባት ይሰጣል፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያ ዙር እና በሁለተኛ ዙር በአጠቃላይ 5.8 ሚሊዮን በላይ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ይከተባሉ፡፡
ፕሮፌስር ስለሺ ጋሮማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ በፖሊዮ ዘመቻ ማስጅመሪያ ፕሮግራም የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በመንግስት በኩል የሕጻናትን ጤንነት ለማሻሻል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን፣ የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ እንዲጠፋ በሚደረገው ዘመቻ ትኩረት በመስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሁሉም ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመተባበር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በጤና ሚኒስቴር ስም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኡጁሉ ኦዶል የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት የፕሬዘዳንት ተወካይ በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ክልሉ የፖሊዮ ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሁሉም ወረዳዎችና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በሚደረገው ክትባት ዘመቻ ፖሊዮን ጨርሶ ለማጥፋት በክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ ስራ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ዘመቻ መሳካት ወላጆች፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማገሌዎች፣ የትምህርቱ ማሕበረሰብ እና ሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ሚኪያስ አልዩ ባደረጉት ንግግር አገራችን ፖሊዮን ጨርሶ የማጥፋት ንቅናቄ ከተቀላቀለችበት እ.ኤ.አ ከ1996 ጀምሮ የፖሊዮ ማጥፋት እስትራቴጂዎችን በመዘጋጀት አመርቂ ወጤቶችን ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሰው፤ በክትባት እጥረት ምክንያት እየተከሰተ የሚገኘውን የፖሊዮ ወረርሽኝ ጨርሶ እስኪጠፋ ኢንስቲትዩቱ እደረገ ያለውን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እና የክትባት ዘመቻው በተሳካ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አቤል አሰፋ የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊና ሌሎችም የአጋር ድርጅት ተወካዮች በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ወቅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የተለያዩ የቅኝት ጥናቶችና መረጃዎች በመድረኩ ቀርበው ውይይት ከመደረጉም በላይ የክትባት ዘመቻው ከህዳር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም ለ4 ተከታታይ ቀናት በቤት ለቤት ጉብኝት የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ ፖሮግራሙ ተጠናቋል፡፡