የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በተገኙበት መስከረም 27/2017 ዓ.ም በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በክትባት እጥረት ምክንያት የተከሰተውን የፖሊዮ በሽታ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የክትባት ዘመቻውን በይፋ ለማስጀመር ያለመ ነው፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ደረጃ ከፍተኛ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፖሊዮ ቅኝት ስራዎችን እና የወረርሽኝ ምላሽ ስራዎችን አጠናክሮ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ላለፉት በርካታ ዓመታት የፖሊዮ ቅኝት እና ወረርሽኝ ምላሽ አፈጻጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡት መስፈርቶች ተለክቶ ኢትዮጵያ ከሚጠበቀው እስታንዳርድ በላይ እየተገበረች ትገኛለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ መጥፋቱ በአፍሪካ ሰርተፊኬሽን ኮሚቴ የተረጋገጠ ቢሆንም በክትባት እጥረት ምክንያት የሚመጣ የፖሊዮ ወረርሽኝ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋት ሆኖ በመቀጠሉ አሁን በሚካሄደው ክትባት ዘመቻ ክትባት ያለፋቸው እና ጀምረው ያቋረጡ ህጻናትን የመለየትና ወደ ክትባት ጣቢያዎች ሄደው እንዲከተቡ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በክትባት እጥረት የሚመጣ የፖሊዮ ታማሚዎች ሪፖርት ከተለያዩ ቦታዎች የተገኙ ሲሆን ወረርሽኙ በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአፋር፣ በአማራ እና በጋምቤላ ክልሎች ወረርሽኙ የተከሰተ ሲሆን እነዚህን ከልሎች ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ክትባቱን የወሰዱም ሆኑ ያልወሰዱ በአጠቃላይ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሚያቸዉ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ያሲን ሐቢብ የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ የእንኳን ደሕና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ፕሮፌሰር ቦጋለ ወርቁ የኢትዮጵያ የፖሊዮ የማጥፋት ሰርተፍኬሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ዶ/ር ኦውን ኤል ካልዋ የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ የአጋር ድርጅቶችን በመወከል ክትባቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ,ክቡር አሊ መሐመድ የአፋር ክልል በምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ የክትባት ዘመቻውን በይፋ በመክፈት አስጀምረዋል፡፡
የክትባት ዘመቻው ከመስከረም 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በቤት ለቤት ጉብኝት ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ከማስጀመሪያ ፕሮግራሙ መረዳት ተችሏል፡፡