የአሜሪካው አምባሳደር ኢንስቲትዩቱን ጐበኙ

የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥራ ጉብኝት አደረጉ
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ አምባሳደር ክቡር ኤርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመገኘት ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ያሉትን የሕብረተሰብ ጤና ሥራዎች ጎበኙ።
አምባሳደሩ በኢንስቲትዩቱ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት፤ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከልን፣ የሕብረተሰብ ጤና ብሔራዊ ላቦራቶሪዎችን እንዲሁም የጤና ምርምር ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በጉብኝቱም ወቅት ኢንስትቲዩቱ ከተመሠረተበት እ.አ.አ 1924 ጀምሮ ባለፉት 100 ዓመታት ጉዞ እና የዕድገት ደረጃዎችን አብራርተዋል። ዶክተር መሳይ አክለውም፣ ኢንስቲትዩቱ አንጋፋ የሀገሪቱን የሕብረተሰብ ጤና ተቋም እንደመሆኑ መጠን፤ በህሕብረተስብ ጤና ሳይንሳዊ ምርምር፣ በላቦራቶሪ አገልግሎት፣ በበሽታዎች ቅኝት እና በወረርሽኝ መከላከል ዙሪያ የኢትዮጵያውያንን እና የአለምን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ሀላፌነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ እያከናወናቸው ባሉት ዘመናዊና ስልታዊ ሥራዎች የአህጉሪቱ “የልህቀት ማዕከል” (Center of Excellence) መሆኑን ማየታቸው እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል። የአሜሪካ መንግሥት ለረጅም ዘመናት ወዳጅ ለሆነችው ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እንዲኖራት ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ ያሳወቁት አምባሳደሩ፤ በሁለቱ ወገኖች የጋራ ትብብር የተከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ስኬታማ ውጤት ማስመዝገባቸውን በመጥቀስ፣ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነትና ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።