የአዳዲስ ክትባቶች ትግበራ ግምገማ ለመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና….

በኢትዮጵያ የአዳዲስ ክትባቶች ትግበራ ግምገማ ዙሪያ የመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ተካሄደ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክትባት የሚከላከሉ በሽታዎች ዲቪዥን አስተባባሪነት፣ Integrated Post-Introduction Evaluation (PIE) in Ethiopia የመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ከሰኔ 1-5 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል ተካሂዷል።

ስልጠናው በቅርቡ ወደ አገሪቱ የገቡ አዳዲስ ክትባቶችን አፈጻጸም በመገምገም የተገኙ ተሞክሮዎችንና ተግዳሮቶችን ለመለየት እና ለወደፊት የክትባት ፕሮግራሞች ማሻሻያ ግብዓት ለማግኘት ያለመ ነው።
በመክፈቻው ላይ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገመቹ ታደሰ የክትባት በሽታዎች ምርምር የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ ይህ ጥናት ከስትራቴጂው ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ለማንኛውም ጥናት የመረጃ ጥራት ወሳኝ በመሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች በኃላፊነትና በጥንቃቄ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስቴር የክትባት አገልግሎት ሃላፊ አቶ መልካሙ አያሌው በበኩላቸው፣ ጤና ሚኒስቴር ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የክትባት ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርብ ጊዜ የገቡትን የሄፓታይተስ ቢ፣ የወባ እና የኩፍኝ ክትባቶች አፈጻጸም ለመገምገም የሚሰበሰበው መረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የክትባት የሚከላከሉ በሽታዎች ምርምር ዲቪዥን ሃላፊ ዶ/ር ራጂሃ አቡበከር ደግሞ ተሳታፊዎች በስልጠናው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱን በተገቢው ሁኔታ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ከስልጠናው በኋላ ሰልጣኞቹ ለ15 ቀናት በተመረጡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመሰማራት የመስክ መረጃ ስብስብ ሥራ ያከናውናሉ።