የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የSimulation Exercise

የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተግባር ልምምድ (Simulation exercise) አካሄዱ፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል በተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (DRC) እና በዩጋንዳ አገራት የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ዝግጁነት ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር የመግቢያና መውጫ የጤና ቁጥጥር ባለሙያዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የጤና ልየታ፣ የቁጥጥር፣የቅኝት ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ተግባራዊ ልምምድ አካሄዱ፡፡
የተግባር ልምምዱ (Simulation exercise) ዋና ዓላማ የግብዓትና የሰው ኃይል ዝግጁነት ክፍተት በመለየት በሽታው ወደ አገር እንዳይገባ የመከላከል እንዲሁም በሽታው ቢከሰት እንኳን የመከላከል እና የምላሽ ስራዎች በምን ያህል ደረጃ ውጤታማ ይሆናሉ፣ ምን ጠንካራ ጎኖች አሉ፣ ክፍተቶችስ ምን ይመስላሉ የሚሉትን በመለየት በቀጣይ መስተካከል ያለባቸውን በማስተካከል ጠንካራ ዝግጁነትን ለማረጋገጥ ነው፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በተግባር ልምምዱ የማጠቃለያ ግምገማ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱን እና የተግባር ልምምድ መካሄዱ ትልቅ ተግባር መሆኑን አድንቀው፣ ከዚህ በፊት የነበሩትን ልምዶችና አሁን የተገኘውን እውቀት መሰረት በማድረግ በቀጣይ እስከ ታችኛው የጤና ተቋምና የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች በማውረድ ሁሉም ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ አገራችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ሕብረተሰባችንን ከማንኛውም የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ችግሮች በመጠበቅና በመታደግ ለትውልድ የሚሻገር ስራ በመስራት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተግኝተው በተግባር ልምምዱ ወቅት እንደገለጹት ኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (DRC) እና በዩጋንዳ አገራት ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከልን ጥብቅ የሆነ የቅኝትና የልየታ ስራ እንዲሰራ የተደረገ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ባሉ በአየርም ሆነ በየብስ በሚገኙ የመግቢያና መውጫ በሮች በኩል በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት የሚመጡ ተጓዦችን የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥርና ቅኝት ስራዎችን ተጠናክረው እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ማንኛውንም የተላላፊ ወረርሽኝ በሽታ ናሙናዎች ለመመርመር የሚያስችል የሪፈረንስ እና የሪፈራል የላቦራቶሪ ዝግጁነት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በኢትዮጵያ የኢቦላ ቫይረስ ተጠርጣሪ የሌለና በሽታውም ወደ ሀገር ያልገባ መሆኑን አረጋግጠው፣ በሽታው ሊከሰት ቢችል እንኳን ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙዎች የተግባር ልምምድ በማድረግ የክህሎት እና የብቃት ደረጃቸውን ያሳደጉ በመሆኑ በበሽታው የተጠረጠረ ሰው ቢገኝ ወደ ሌሎች ሰዎች በሽታውን ሳያስተላልፍ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች በመውሰድ አስፈላጊውን ህክምና የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰጡ መልዕክቶችን በሚገባ በመከታተል ተግባራዊ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ለመከላከልና ዝግጅትን ከማጠናከር አንጻር ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው አገራት አውሮፕላን ወደ አገራችን በረራ ከማድረጉ አስቀድሞ እያንዳንዱ ተሳፈሪ የጤና መረጃ ከመሙላት (e-THDF) አንስቶ እስከ መጨረሻው መደረግ የሚገባቸውን የቅኝት፣ የልየታ እና ክትትል ስራዎች በሚገባ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተካሄደው የጤና ባለሙያዎች የተግባር ልምምድ ወረርሽኙን በመከላከል ደረጃ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ለማስቀጠል፣ ክፍቶችን ደግሞ በማረምና በማስተካከል በዝግጁነት በኩል ያሉ ተግባራት አስተማማኝ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የተከናወነ መሆኑን ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
አቶ ተመስገን ለሚ የኢንስቲትዩቱ የተጓዦችና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኢቦላ ቫይረስ ምንነት ሲያስረዱ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በ DRC እና Uganda አገራት የተከሰተው የኢቦላ በሽታ Bundibugyo Ebola Virus አማካኝነት የሚመጣ እጅግ ከባድና ለህልፈተ ህይወት የሚዳርግ ተላላፊ በሽታ ሲሆን በሽታው ፈጣን ህክምና ካላገኘ የሞት ምጣኔው እስከ 90% ሊደርስ የሚችል በጣም አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑን፣ ምልክቶቹም ድንገተኛ ትኩሳት፣ ከፍተኛ የጡንቻና የራስ ምታት፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥ እና ከውስጥና ከውጭ አካላት የሚወጣ የደም መፍሰስ (Hemorrhage) የመሳሰሉት ምልክቶች መሆናቸውን ጠቁመው በሽታው ወደ አገር እንዳይገባ በሁሉም የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና የየብስ መግቢና መውጫ በሮች ላይ በተለይም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከፍተኛ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሁሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ከበበው በቀለ በአትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዳይሬክተር የሕረተሰቡን ጤንነት ከማስጠበቅ አንጻር አየር መንገዱ እየሰራ ያለውን በተመለከተ ሲገልጹ የአደጋ ጊዜ የምላሽ ዝግጁነት ተግባራትን አንዱ የስራችን ክፍል በማድረግ እቅድ ወጥቶ፣ አፈጻጸሙንም በየጊዜው እየተገመገመ መሆኑንና የህብረተሰቡን ጤና ችግር የሚፈጥሩ ተላላፊ በሽታዎችንም ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ከኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት አስፈላጊውን ስራ ሁሉ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ምናባዊ የሆነ የኢቦላ ተጠርጣሪ ሰው በማዘጋጀት በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት ጀምሮ መረጃዎችን በማዘጋጀት እስከ ለይቶ ማቆያ ድረስ መደረግ ያለባቸውን አስፈላጊ ተግባራት ሁሉ ያካተተ የተግባር ልምምድ ያካሄዱ ሲሆን በልምምዱ ወቅት የነበሩ ጠንካራ ጎኖች እና ክፍተቶችን ተለይተው የማስተካከያ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ የቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፥ NISS, Immigration, Customs, Federal Police, እንዲሁም አጋር ድርጅቶች፡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የአሜሪካ በሽታዎች መከላከል ማዕከል (US CDC) ፣ የዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ፥ UK HSA እና ሌሎችም የተግባር ልምመዱ ላይ በአካል በመገኘት የገንዘብ ፥የእውቀት እና የክህሎት ድጋፍ አድርገዋል፡፡