የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ በኢትዮጵያ የቅድመ ዝግጁነትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ተካሄደ

በአንድ አንድ የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ በኢትዮጵያ የቅድመ ዝግጁነትና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ
በአንድአንድ የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ የቅድመ መከላከልና የዝግጁነት ሥራዎችን ለማጠናከር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ ሆስፒታሎች የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) የአንድ አንድ የአፍሪካ ሀገራት የኢቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ካሳወቁበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ የዝግጁነት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነዒማ ዘይኑ፣ በሽታው እስካሁን በኢትዮጵያ ባይከሰትም በሌሎች ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታውሰዋል። በመሆኑም ወረርሽኙ ወደ ሀገራችን እንዳይገባና ከተከሰተም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ የቅድመ መከላከልና የዝግጁነት ሥራዎችን ከወዲሁ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል። ዳይሬክተሯ አክለውም ሁሉም ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመሥራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የመድረኩ አስተባባሪ እና የፈጣን ምላሽ ቡድን አስተዳደር ዲቪዥን ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አስራት በበኩላቸው፣ ጥሪውን አክብረው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተገኙት ተሳታፊዎች ላይ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። የኢቦላ ቫይረስ እንደ ሀገር ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለከቱት ዶ/ር መልካሙ፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ቀጣይነት ያላቸው ሥልጠናዎችና የተጠናከሩ የዝግጁነት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።