የኢትዮጵያ የስነ-ምግብ ፖሊሲዎችን ለማጠናከር የተሻሻለው የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥን መመሪያ ተመረቀ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የኢትዮጵያ የምግብ የንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የስነምግብ ባለሙያዎች እና አጋር ድርጅቶች በተገኙበት በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡
በዚህ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥ የምርቃት ስነስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች እና የስነ-ምግብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።ይህ መመሪያ ለህብረተሰብ ጤና መሻሻል፤ ለሥነ-ምግብ እቅድ ዝግጅት፣ እንዲሁም በርካታ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ፖሊሲ አወጣጥ ላይ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እንዲያወጡ እገዛ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም ፋውንዴሽን መስራች እና ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በምግብ ሠንጠረዥ መፅሐፉ ምርቃት ላይ እንዳሉት ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የምግብ እጥረትን ለማስወገድ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ የነበሩ ሲሆን ይህ ሠንጠረዥ ደግሞ ለምግብ ስርዓቱ መሻሻል የሚኖረው አስተዋጽዖ በጣም ከፍተኛ ነው።
ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ መመሪያና መጸሀፉን በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የምግብ ስብጥር መረጃ ከምግብ-ተኮር የአመጋገብ መመሪያዎች እስከ ማጠናከሪያ ስልቶች እና የስነ-ምግብ አገራዊ ፖሊሲዎች ድረስ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም ጤናማ አመጋገብን እና ጠንካራ የምግብ ስርዓትን ለማስፈን ይህ የኢትዮጵያ የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥ ያለው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥ በተለያዩ የምግብ አይነቶች ላይ አጠቃላይ እና ወቅታዊ የትንታኔ መረጃዎችን በዝርዝር እንደሚያቀርብ ገልጸው ፣ ባህላዊና ሀገር በቀል ምግቦች፣ ሀገር ውሰወጥ የሚዘጋጁና ተዘጋጅተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዲሁም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰብሎች ላይ ምርምር እና ጥናቱ በጥልቀት መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ይህ የተሻሻለው የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥ አዳዲስ የንጥረ-ምግብ እሴቶችን እና መካተት ያለባቸውን ሁሉ በመጨመር የረዥም ጊዜ የመረጃ ክፍተቶችን የሚፈታ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፣ ይህ የብሄራዊ የምግብ አዘገጃጀት መጽሀፍ እና ድረ-ገጽ ላይ የተመሰረተ የመረጃ ቋት ኢትዮጵያ የአመጋገብ እና የህዝብ ጤና ውጤቶችን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚደግፍ አብራርተዋል።
ክብርት ወ/ሮ አለምፀሃይ ሰርገዊ በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ስነ-ምግብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ የተሻሻለው የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥን መመሪያ በ ምርት አያያዝ እና የምግብ ደህንነትን በማጠናከር ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ አለምፀሃይ አያይዘውም መጽሀፉ ምግብ በሚበስልበት ወቅት የንጥረ-ምግብ ማዕድናትን ለማቆየት እንዴት እንደሚቻል እንዲሁም ምግብ ይዘቱን በማድረቅ ፣በማከማቸት ፣በማቀነባበር እና በማብሰል ጊዜ እንዴት እንደሚለውጥ ብሎም ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ ባሉት የእዝ ሰንሰለቶች ጊዜ የአመጋገብ ዋጋን ለመጠበቅ የሚረዱ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እና አሰራሮችን የሚደግፉ ቪታሚኖች እና ማዕድናት እንዴት እንደሚለወጡ ግንዛቤዎችን እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
በዚህ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ቅንብር ሠንጠረዥ የምርቃት ስነስርዓት ላይ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ጌትስ ፋውንዴሽን እና ያዳም ፋውንዴሽን ሃላፊዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዘርፉ በቀጣይ እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።