የኢኒስቲትዩቱ የስራ ኃላፊዎች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጎበኙ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (ደኢህጤኢ) የስራ እንቅስቃሴን በቴክኒክ ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገለጹ።
ዶ/ር ጌታቸው በትላንትናው ዕለት የመሩት የኢህጤኢ አመራር ቡድን ባደረገው የስራ ጉብኝት እንዳስታወቁት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ ለተቋቋመው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ሃላፊነት አለበት ብለዋል። “ክፍተቶቻችሁን ለበማሟላት ረገድ የምታደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ ነን። በስራ ባልደረቦቻችን የሚሰጡት የቁሳቁስና የስልጠና ድጋፎች ከጎናችሁ ለመቆም ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያሉ፣” ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት ሁለት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እና የገመድ አልባ የኢንተርኔት መጠቀሚያ(ዋይ-ፋይ ሞባይል አፓራተሶችን) ለደኢህጤኢ ካስረከቡ በኋላ ነው። በስነ-ምግብ፣ አካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት የተደረገው ልገሳና የእውቀት ሽግግር ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። “የሥርዓተ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር እና ብሔራዊ የሥርዓተ-ምግብ መረጃ ማዕከል ከእናንተ ጋር በትብብር ለመስራት ተነሳሽነቱን ይወስዳል። ይህ ጥሩ ጅምር ነው። በጤናው ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የጋራ ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።”
ዶ/ር ጌታቸው ደኢህጤኢ ከሌሎች የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ሰፊ ልምድ በመቅሰም ተጠቃሚ መሆን አለበት ብለዋል። “በአማራና በትግራይ ክልል ያሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች በዘርፉ ጠቃሚ ልምድ አላቸው። ወደ እነዚህ ክልሎች የልምድ ልውውጥ ጉብኝት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። ኢህጤኢ ለደኢህጤኢ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ይህንን ተነሳሽነት ለመደገፍ ዝግጁ ነው። በቅርቡ በሁለቱ ተቋማት መካከል በአመራር ደረጃ ተጨማሪ ውይይት ይደረጋል፣” ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የደኢህጤኢ ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ አጉኔ አሾሌ የፌዴራል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተቋማቸውን ለመደገፍ የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል። “እንደ ኢንስቲትዩት አዲስ የተቋቋምን ነን። ከኢህጤኢ እና ከክልላዊ ተቋማት ትልቅ ድጋፍ እንፈልጋለን። ከእናንተ ከዚህ የበለጠ ትብብርም እንጠብቃለን። ለመጠናከር በምናደርገው ጥረት እባካችሁን ደግፉን፣”*ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ፣ አጉኔ ተናግረዋል።
የስርዓተ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ፥ ለደኢህጤኢ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። “በአቅማችን መርዳት የኛ ኃላፊነት ነው። ያቀረብነው የመጨረሻው ድጋፍ አይደለም። የቴክኒክ እና የቁሳቁስ ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን። ላፕቶፖች ኮምፒዩተሮቹን ዳታ ኤክስፐርቶቹ የደኢህጤኢን የምርምር ጥረቶች እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል ብለን እናምናለን፣” ሲሉ ዶ/ር ማስረሻ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የብሔራዊ የሥርዓተ-ምግብ,መረጃ ማዕከል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ፣ ዶ/ር አረጋሽ ሳሙኤል እንደተናገሩት ለደኢህጤኢ የተሰጠው የዕውቀት ሽግግር ስልጠናና የላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ድጋፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ የተቋቋመው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያበረታታ ነው። “ተጨማሪ የግብአት እና የእውቀት ሽግግር ድጋፎችን ለማቅረብ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፣” ሲሉ ተናግረዋል።