የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በመንግስት እና በጤናው ዘርፍ የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሄዱ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በመንግስትና በጤናው ዘርፍ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ በተገኙበት ሚያዝያ 8/2017 ዓ.ም ተወያዩ።
ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ የውይይቱ መጀመሪያ ላይ እንደገለፁት ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ሀገር በተለያዩ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንና በቀሩት ሦስት የበጀት ዓመቱ ወራትም ይበልጥ የላቀ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት የውይይት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ አጠቃላይ የአፈፃፀም ሪፖርቱን አቅርበው በቀጣይም በጤናው ዘርፍ ይበልጥም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ተግባራትን አስቀምጠዋል።
በቀሩት የበጀት ዓመቱ ወራትም፤ የታቀዱ ተግባራትን በትጋትና በላቀ ደረጃ መፈጸም፣ የሪፎርም ስራዎችን በፍጥነት መፈጸም፣ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ መከላከልና መቆጣጠር ላይ መረባረብ፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ሀብትን በውጤታማነት መጠቀም፣ የጤና መረጃዎችን በዲጂታል ስራዎች ማጠናከር፣ አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን በማፋጠን መተግበር ላይ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ከመድረኩ ተገልጿል።