የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች የሠራተኞች ጤንነትና ደህንነት ስልጠና ስለጠኑ

የሠራተኞች ጤንነትና ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ ተገለጸ፤ 30 የሚሆኑ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ስልጠና አጠናቀው ተመርቀዋል::
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር በመጀመሪያ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ያሰለጠናቸውን 30 ባለሙያዎችን ዛሬ በይፋ አስመርቋል።

በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሥራ አካባቢ ደህንነት እና ጤንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በተከናወነው በዚህ ፕሮግራም ላይ፤ ለሠራተኞች በመሰረታዊ መጀመሪያ ዕርዳታ ዙሪያ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ማስጨበጥ ጤናማና ምቹ የሥራ ቦታን ለመፍጠር ትልቅ መሠረት መሆኑ ተገልጿል። ይህም ለሠራተኛው ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ውጤታማነትም ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢንስቲትዩቱ የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እልፍአገር ተተካ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ አደጋዎች ቀድመው እንዲጠነቀቁና አደጋ ቢደርስ እንኳን ፈጣንና ትክክለኛ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲችሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን አብራርተዋል።
“የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ጉዳይ ከሠራተኞች የሥራ ውጤታማነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በሠራተኞች አዋጅ እና መመሪያዎች ላይ ተካቶ እየተሠራበት ይገኛል” ያሉት ወ/ሮ እልፍአገር፤ ከዘወትር ሥራዎች ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመከላከል ቅድመ ጥንቃቄን የዘወትር ልምድ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተወካይ አቶ ከበደ እንዳልካቸው በበኩላቸው በመሰረታዊ የመጀመሪያ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ሰፊ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን፤ ኢንስቲትዩቱ ለሠራተኞቹ ደህንነት ትኩረት በመስጠት ይህንን ሥልጠና ማዘጋጀቱ የሚደነቅ ተግባር መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። አቶ ከበደ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን በማጣቀስ መሠረታዊ የሕይወት ክህሎት ትምህርት ያካፈሉ ሲሆን፤ በዕለቱ ተመራቂዎች አማካኝነትም ተግባራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ አሰጣጥ ሂደት ለታዳሚው ቀርቧል።
በተጨማሪም ስለ ደህንነት ሳይንሳዊ መሠረታዊ እሳቤዎችና አተገባበሮች በአቶ ታደሰ ገረመንፈስ አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ቀርቦ የጋራ ውይይት ተካሂዶበታል።
ኢንስቲትዩቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባከበረው በዚህ ዓለም አቀፍ የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ቀን መርሃ ግብር ማጠቃለያ ላይ፤ ሥልጠናቸውን ላጠናቀቁ 30 ሠራተኞች የሰርተፊኬትና የዕውቅና አሰጣጥ እንዲሁም የቃለ-መሐላ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።