የኢንስቲትዩቱ አመራሮች የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎበኙ

በጉብኝቱ ወቅትም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደተናገሩት – የንግስት እሌኒ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአካባቢውን ማህበረሰብ እና በሪፈራል የሚመጡ ታካሚዎችን የጤና ችግሮች ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት እና እየታዩ ያሉ ለውጦች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዉ፤ በላብራቶሪ አገልግሎት አቅምን በማጠናከር በኩል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠንካራ አደረጃጀት ከመፍጠር ጀምሮ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በመላ ሀገሪቱ ከ5ሺ በላይ ላብራቶሪዎችን እንዲሁም ከ40 በላይ ሀገርአቀፍ የላብራቶሪ ማእከላትን እየደገፈ መሆኑን አውስተው ለንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም የላብራቶሪ አገልግሎት እንዲጠናከር ድጋፎች እየተደረጉ እንዲሁም በትብብር ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር መሳይ ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳበ የተከበሩ ዶ/ር ታደለ ቡራቃ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቃቸው የነበሩ የላብራቶሪ አገልግሎቶች በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትኩረት አግኝተው ምላሽ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸዉ ገልጸው በመላ ሀገሪቱ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችም የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል::
በጉብኝቱ ወቅት የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክሴኩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ይድነቃቸው ደዳቸው እንደተናገሩት ሆስፒታሉ በተለያዩ ስያሜዎች ከ40 ዓመታት በላይ የህብረተሰቡን የጤና ችግሮች ለመፍታት ሲያገለግል መቆየቱን ተናግረው ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል::
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮን አብደላ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ኢንስቲትዩቱ ለሆስፒታሉ ሲያደርግ በነበረው የላብራቶሪ አገልግሎትን የመደገፍ ስራ ውጤቶች በመታየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ክትትልና ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በጉብኝቱ በተመለከቱት ስራ መደሰታቸውን ገልጸው በሆስፒታሉ በርካታ ምሁራን በመኖራቸው በዘርፉ ለሚደረጉ የምርምር ስራዎች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በምርምር ዘርፍ እገዛ እንደሚያደርግ እና በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትን በመወከል የሆኑት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤርሚያስ ሞሊቶ ለተደረጉ ድጋፎች በዩኒቨርስቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
በተጨማሪ የማእከላዊ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሆሳና ቅርንጫፍ ላብራቶሪንም ጉብኝዎቹ ተመልክተዋል::