የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በማርበርግ ቫይረስ በሽታ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ምልከታ አደረጉ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትበኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመገኘት በማርበርግ ቫይረስ በሽታ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በጂንካ ከተማ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የህብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከክልል ጤና ቢሮዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ የሙያ ስብጥር ያካተተ ከፍተኛ ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን በማደራጀት በሽታዉን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል::
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የማህበረሰብ አቀፍ የቅኝት ስራዎች፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማከም፣ ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ንክኪ ያላቸዉን ሰዎች የመለየት ስራዎች በመሰራት ላይ እንዳሉ ያብራሩ ሲሆን በተጨማሪም በብሔራዊ እንዲሁም በክልል ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የክስተት አስተዳደር ስርዓት (Incident Management System) ተቋቁሞ የፈጣን ምላሽ ስራዎችን በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል::
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ታደለ ቡራቃ፣ የመስክ ምልከታው ዓላማ የማርበርግ በሽታን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር በተጨባጭ ምን እየተሰራ እንደሆነ በተጨባጭ ለማየት መሆኑን ገልጸዋል።
በሽታውን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው በመላው አገሪቱ ምን ላይ እንዳለ እና ተደራሽነቱንም ለማረጋገጥ መሆኑንም አንስተዋል።
የተከበሩ ዶ/ር ታደለ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከመስራት ተያይዞ ለማከምና ለመከላከል እንዲሁም የሰው ኃይል ዝግጅትና የግብዓት አቅርቦት እንደተቋም አቅዶ በመስራትና በማዘጋጀት የተሰራውን ስራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል::
በሽታው ድንበር ተሻጋሪ ከመሆኑ አንጻር በድንበር አካባቢ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም ድንበር አካባቢ የቅኝት ስራ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት የገለጹት የተከበሩ ዶ/ር ታደለ፣ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን የመለየት እና ወደ በህክምና ማቆያ የመላክ እንዲሁም በላብራቶሪ የመለየት ስራ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል::