የካውንት ዳውን 2030 ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል

የዘላቂ ልማት ግቦችን (Sustainable Development Goals 2030 /SDG/) መነሻ በማድረግ በመላው አፍሪካ የሚገኙ የጤና መረጃዎችን፣ የእናቶች እና የህፃናት ጤና አፈጻጸምን ለመገምገም የተዘጋጀው “ካውንትዳውን 2030” (Countdown 2030) የተሰኘው አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ከ36 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ ኢትዮጵያ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ያስመዘገበችውን ፈጣን ለውጥ አብራርተዋል። ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ ባደረገችው የተቀናጀ ጥረት የእናቶች ሞት ምጣኔን በ100 ሺህ በህይወት ከሚወልዱ ህፃናት ውስጥ ወደ 141 ዝቅ ማድረግ የቻለች ሲሆን፣ ይህም በአህጉር ደረጃ ካሉ ምርጥ ተሞክሮዎች አንዱ ነው። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል (Africa-CDC) መቀመጫ መሆኗ፣ አህጉራዊ ድንበር ዘለል የጤና ስጋቶችንና ወረርሽኞችን በጋራ ለመከላከል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው መረጃ በማመንጨትና እንደ ማርበርግ ቫይረስ በሽታ እና ኤምፖክስ ያሉ አደገኛ በሽታዎችን በፍጥነት በመለየት ረገድ የዳበረ አቅም እንዳለው ገልጸው ይህም አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ሀገር-በቀል የጤና መረጃ ባለቤትነት በመሸጋገር ላይ እንደሚገኙ ማሳያ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር መሳይ በሳምንቱ ውስጥ የሚከናወኑት የቴክኒክ ስራዎች በመረጃ ትንተና ላይ የዘመኑ መገልገያዎችን እና ዘዴዎችን በመጠቀም የቴክኒክ ክህሎትን ማሳደግ፣ ጥራት ያላቸው የትንታኔ ሪፖርቶችን ማውጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በመፈተሽና ተሞክሮዎችን በመካፈል በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እና መረጃዎች ከፖሊሲ ግብአትነት ወደ ተግባር መተርጎማቸውን ማረጋገጥ ከጉባኤው አላማዎች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ በዝርዝር አብራርተዋል።
የ“ካውንትዳውን 2030” ዳይሬክተር ዶ/ር ቼኪህ ፋይ፣ ይህ ስብስብ የቴክኒክ ትንታኔን ከአመራር ቁርጠኝነት ጋር ያቀናጀ መሆኑን ገልጸው፣ ዋናው ዓላማው የተሻለ መረጃን ወደተሻለ የፖሊሲ ውሳኔና ውጤት መቀየር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው እስከ ሳምንቱ መጨረሻ የሚቀጥል ሲሆን፣ ሀገራት እስከ 2030 በቀሩት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ ሊያከናውኗቸው በሚገቡ ስልታዊ ኢንቨስትመንቶች ላይ የጋራ መግባባት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።