የክልል የጤና የደህንነት አቅም ምዘና ማካሄድ ለአገርዊ የጤና ደህንነት ግንባታ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም ዓቀፍ ጤና ደንብ እና የአንድ ጤና ጽ/ቤት ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ እና ከዩኒይትድ ኪንግደም የጤና ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የኢንስቲትየቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በተገኙበት ሁሉን አቀፍ የሆነ በክልል ደረጃ የጤና ደኅንነት አቅምን ለመመዘን የሚያስችል ማዕቀፍ ከመጋቢት 9 እስከ 12/2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና ዓለማ በክልል ደረጃ የጤና ደኅንነት አቅምን ለመገምገም ብሎም በተለዩ ክፍተቶች መሰረት የክልሎችን አቅም ለመገንባት የሚያስችል የጤና ደህንነት ዕቅድ ለማዘጋጀት ያለመ ነው፡፡ በዚህ አውደ ጥናት ረቂቅ የመመዘኛ ሰነድ (JEE tool) የክልሎችን ኃላፊነት ባገናዘበ መልኩ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት እንደ ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች (2005) (IHR) መሰረት የጤና ደኅንነት አቅምን የሚገመግም ማእቀፍ (Tool)፣ ለአንድ አገር እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም አገራችን ያለችብትን የአቅም ሁኔታ በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባሉ 12 ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የጤና ደኅንነት አቅምን ለማጎልበት የጋራ የውጭ ግምገማ (JEE) መመዘኛ ሰነድን የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እንደ አገር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዚህ ረገድ አጽንኦት እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ ብሄራዊ የጤና ደህንነትን ለማጠናከር ክልሎች በዚህ በኩል ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ በኢንስቲትዩቱ የዓለም አቀፍ ጤና ደንብ እና የአንድ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው እንደ አገር ብሔራዊ ጤና ደህንነት አቅምን በባለፈው ዓመት በመስከረም ወር መካሄዱን አውስተው፤ በዚህ አውደ ጥናት ላይ የክልሎችን ተግባርና ኃላፊነት መሰረት ባደረገ መልኩ የጤና ደህንነት መመዘኛ ማዕቀፉ በክልሎች፣ በሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም በአጋር አካላት ተሳተፎ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያ ይህንን ምዘና በክልሎች ስታካሂድ ከናይጂሪያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሀገር እንደምትሆን አንስተዋል፡፡ እንዲሁም ክልሎችን በሁለት ደረጃ (two phases) ተከፋፍሎ ምዘናው እንደሚከናውን አስታውቀዋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የዩኒይትድ ኪንግደም የጤና ኤጀንሲ (UKHSA) እና የሪሶለቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ (RTSL) ተወካዮች አውድ ጥናቱን አስመልክቶ የየራሳቸውን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመቀጠልም በክልል ደረጃ ምዘናው ሲካሄድና የክልል የጤና ደህንነት እቅዶች ሲዘጋጁ የቴክኒክና የፋናነስስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አጋርነታቸውን አሳውቀዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር፣የግብርና ሚኒስቴር፣የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን፣ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ የግብርና ባለስልጣን፣የእንሰሳት ጤና እንስቲትዩት፣ የሁሉም ክልል ተወካዮች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በአውደ ጥናቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡