የኮቪድ-19 ፓክስሎቪድ (Paxlovid) ማከሚያ መድሐኒት ውጤታማነቱ ተገመገመ
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከልና ምላሽ መስጠት ዳይሬክቶሬት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 ዲቪዥን ከጤና ሚኒስቴርና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፓክስሎቪድ (Paxlovid) የተባለ የኮቪድ-19 በሽታን ለማከም የሚያስችል መድሃኒት በአራት ክልሎች በተመረጡ 17 የጤና ተቋማት ላይ እየተካሄደ የሚገኘውን የሙከራ አፈጻጸም እና የተመዘገቡ ውጤቶችን አስመልክቶ ጥቅምት 19 እና 20/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የግምገማ መድረክ አካሄደ፡፡
የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ ለ11 ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውን የኮቪድ-19 በሽታን ለማከም ተፈጻሚ የተደረገው መድሃኒት ምን ያህል ጥቅም ላይ ውሏል፣ ወጤታማነቱ ምን ይመስላል፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት፣ በተግባራዊነቱ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው እና በቀጣይ መቀመጥ ያለባቸው አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው የሚሉትን ለመገምገምና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው፡፡
የኮቪድ-19 የማከሚያ መድሃኒት እ.ኢ.አ 2022 በአሜሪካ አገር የተገኘ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ የተካሄደውን መድረክ አቶ አዳነ ወልደአብ የኢንስቲትቱ የኮቪ-19 ዲቪዥን አስተባባሪ በንግግር የከፈቱ ሲሆን ዶ/ር አዳሙ ገላው ከዓለም ጤና ድርጅት በበኩላቸው የኮቪድ-19 የማከሚያ መድሀኒት ትግበራ አጠቃላይ በአለም ዓቀፍ እና በሀገራችን ያለበትን ደረጃ ዝርዝር ሁኔታ አቅርበዋል፡፡
ወ/ሪት ህሊና ፀጋ የኢንስቲትዩቱ የኮቪድ-19 ኬዝ ማኔጅመንት ክፍል አስተባባሪ እንዲሁም የጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተመረጡ17 የጤና ተቋማት ላይ የተካሄደውን የሙከራ ህክምና ውጤታማነቱን፣ የነበሩ ክፍተቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ መፍሔዎችንና በቀጣይ መድረግ የሚገባቸውን አቅጣጫዎች በጽሁፍ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል አቶ መላኩ ገ/ሚካኤል የጃፓይጎ (Jhpigo) ተወካይ ደግሞ የህክምና መድሃኒቱን አስመልክቶ ቅድመ ትግበራ የተካሄደውን የዳሰሳ ጥናት መረጃ በዝርዝር የገለጹ ሲሆን በአጠቃላይ በቀረቡ ሃሳቦች መሰረት በማድረግ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተካሄደው የግምገማ መድረክም የኮቪድ-19 የማከሚያ መድሃኒት በተመረጡት የጤና ተቋማት ተግባራዊ በመደረጉ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው በቀላሉ እንዲያገግሙ ማስቻሉን፣ በዚህም ምክንያት የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉን በመድረኩ የተረጋገጠ ሲሆን በቀጣይም ለተመረጡት ጤና ተቋማት በቂ የሆነ መድሃኒት እና መመርመሪያ ኪት በቅርቡ የሚሰራጭ መሆኑን እና በተለዩ ክፍተቶች ላይ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
አቶ ማንደፍሮ ከበደ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት እና ኢንተለጀንስ ዲቪዥን አስተባባሪ የማጠቃለያ ሃሳቦችን እና በቀጣይ መስተካከልና ተግባራዊ መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣የሆስፒታልና የክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክተሮች እና ባለሙያዎች፣ የተመረጡ መንግስትና የግል ጤና ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም የአጋር ድርጅት ተወካዮች በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡