የወባ ላቦራቶሪ ምርመራ ጥራት ማረጋገጫ ማዕከላትን የሚያግዙ ኮፒውተሮች ለኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ተደረገ

በአይካፕ (ICAP) ኢትዮጵያ አስተባባሪነት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (USAID) በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ ላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ጥራት ማረጋገጫ ማዕከላትን ለማጠናከር የሚያግዙ ኮምፒውተሮች ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና ም/ዋና ዳይሬክተሮች፣ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች የዩኤስኤአይዲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልኡካን እና የICAP የልማት አጋሮች በተገኙበት ጥር 6/2017 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ ርክክብ ተካሄደ፡፡
በአገር ዓቀፍ ደረጃ በሆስፒታሎች እና በጤና ተቋማት የሚሰሩ የወባ ላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቶችን ጥራት የሚያረጋግጡ ማዕከላትን አቅም ማሳደግ ዋና ዓላማው ያደረገው ድጋፍ፣ በአጠቃላይ 175 ኮምፒውተሮች እያንዳንዳቸው ፕሪንተርና ፓወር ሴቭ ያላቸው፣ በገንዘብ ሲተመን 49 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ማወቅ ተችሏል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በርክክብ ፕሮግራሙ ወቅት እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጤና ተቋማት የወባ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ትክክለኛነት የሚረጋገጠው በጥራት ማረጋገጫ ማዕከላት መሆኑን ጠቁመው በድጋፍ የተገኙት ኮምፒውተሮች የጥራት ማረጋገጫ ማዕከላቱን በማጠናከር፣ የወባ ምርመራ ጥራትን በመጨመር የምላሽ ስራዎችን ውጤታማነት በማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ወባን የመቀነስ ግብ ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አይካፕ (ICAP) በኢትዮጵያ ለኢንስቲትዩቱ ወሳኝ አጋር ድርጅት መሆኑን እና በክልል ደረጃ የወባ ላቦራቶሪዎችን አቅም የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ በሚደረገው በርካታ ስራዎች ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ አይካፕ (ICAP) ኢትዮጵያ እና ዩኤስኤአይዲ (USAID)ን ላደረጉት ድጋፍና እገዛ በኢንስቲትዩቱ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ እንዲያጠናክሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ስካት ሆክላንደር የUSAID ኢትዮጵያ ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚታደርገው ከፍተኛ ጥረት፣ ድርጅታቸው USAID አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ረገድ ግንኙነቱን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው፤ የወባ የላቦራቶሪ የምርመራ ውጤት ጥራት ማረጋገጫ ማዕከላት ላይ እየተሰራ ያለውን ውጤታማ ተግባራት አድንቀዋል፡፡
ለርክክቡ የመጡት ልኡካን የኢንስቲትዩቱን ብሄራዊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል እና የወባ ስላይድ ባንክ (Malaria Slide Bank) ጎብኝተዋል፡፡