የውጤት ተኮር አሰራርን ለማጐልበት ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ የሚዛናዊ ስኮር ካርድ ወይም ዉጤት ተኮር ዙሪያ ለተለያዩ ለኢንስቲቲዩቱ የስራ ክፍሎች ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ከመጋቢት 11 እስከ 13/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረክ አካሄደ።
ስልጠናዉ ስለ ሚዛናዊ ስኮር ካርድ ወይም የዉጤት ተኮር ስርዓት ግንባታና ትግበራ ደረጃዎች በቂ ግንዛቤ በመፍጠር በስራ ላይ ማዋል ማስቻል ሲሆን እንዲሁም በዉጤት ተኮር ስርዓት ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ በመያዝ ለሌሎችም ለማስረዳት መቻል ብሎም የዉጤት ተኮር ስርዓት መደበኛ ስርዓት እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
የስልጠናውን አስፈላጊነት በተመለከተ የኢንስቲትዩቱ የዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር አማር በርባ የመክፈቻ ንግግር እና የስራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ ኃላፊ ወ/ሮ የልፍአገር ተተካ በስራ ክፍሉ ስለተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በስራ አስፈፃሚው የሰው ሀብት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ሳራ አዱኛ የለዉጥ ትግበራ እና የዉጤት ተኮር አስፈላጊነት መመሪያ እና በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ባለሙያ አቶ አረጋ ዘሩ የሚዛናዊ ስኮር ካርድና ዉጤት ተኮር ስርዓት ምንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል።