የዓለም የፀረ ተህዋስያን መድሐኒት በጀርሞች የመላመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በሐዋሳ ተከበረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር “እናስተምር፣ እናሳውቅ፣ አሁን እንተግብር” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮውን የዓለም ፀረ ተህዋስያን መድሐኒቶች በጀርሞች መላመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ከህዳር 12-14/2017 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ አካሄደ፡፡
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት የዓለም ፀረ ተህዋስያን የመቋቋም ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማክበር በዘለለ ዓለም አቀፍ የጤና ችግር መሆኑን በመረዳት የሕብረተሰቡን ጤና ችግሮች ለመቀነስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጭምር አውስተው ሀገራችንም ከቅርብ ዓመት ወዲህ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መፍትሄ ለማበጀት ችግሮቹን ለመቀነስ ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ አክለውም ኢንስቲትዩቱም በሀገራችን 16 የፀረ ተህዋስያን ቅኝትና ምላሽ ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በመተንተን፣ በመከላከል፣ በመቆጣጠር፣ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ለዓለም ጤና ድርጅት፣ ለጤና ሚኒስቴር እና ባለድርሻ አካላት መረጃዎችን በማጋራት፣ የብሔራዊና የክልል ላቦራቶሪዎችን አገልግሎትና ጥራት በማሳደግና ተደራሽ በማድረግ፣ ባለሙያዎችን በስልጠና በመደገፍና ተጨማሪ አቅሞችን በመፍጠር የሕብረተሰቡን ጤና ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን እየሰራ ሲሆን ወደፊትም ተጨማሪ 10 የፀረ ተህዋስያን ቅኝትና ምላሽ ጣቢያዎችን በመጨመር፣ በፖሊሲና ስትራቴጂ በተደገፈ መልኩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ በጉልህ እንደተቀመጠው ጤናማ አምራች ኃይል በሌለበት አመርቂ ውጤት ሊመዘገብ ስለማይቻል ኢትዮጵያ እንደሀገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ እንድትመደብ ጤና ላይ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኮንፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ በበኩላቸው የፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ምክንያት ታካሚዎች ለብዙ ቀናት በሆስፒታል እንዲቆዩ እንደሚያደርግ እና የጤና ስርዓቱንም እያዛባ እንደሚገኝ ገልፀው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ጥናቶች በተመራማሪዎች ቀርበው ውይይት የተካሔደባቸው ሲሆን በመጨረሻም የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የመዝጊያ ንግግር ካደረጉ በኋላም የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኮንፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተጐብኝቷል።