የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዣን ካሴያ ኢንስቲትዩቱን ጎበኙ

የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዣን ካሴያ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጎበኙ

የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዣን ካሴያ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፣ መንግሥት የሕብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት፣ የጤና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ እና የድንገተኛ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ የዝግጁነት ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በተለይም የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከልን በማጠናከር በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው፣ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ ከ100 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ተቋም ሲሆን በምርምር፣ በብሔራዊ የላቦራቶሪ አገልግሎት እና በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል።
ዶ/ር ዣን ካሴያ በበኩላቸው በጉብኝቱ ወቅት የተመለከቷቸው የኢንስቲትዩቱ አገልግሎቶችና አቅሞች ውጤታማ መሆናቸውን መመልከታቸውን እና መደነቃቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም በአፍሪካ ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓቶችን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።