የAMR የአምስት አመት ሃገር አቀፍ የትግበራ ዕቅድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ

November 21, 2025
አለም አቀፍ የጸረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ (#AMR) የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በተጀመረበት ህዳር 11/2018 ዓ.ም የአምስት አመቱ ሃገር አቀፍ የAMR የትግበራ ዕቅዱም በይፋ ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የጸረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ አሁንም በኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ከሚታዩ ተግዳሮቶች አንዱ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
እየጨመረ የመጣው ስጋት በአየር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ መሆኑን ጠቅሰው የጤና ስርአታችን፣ ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ እርስ በእርስ ያላቸውን ትስስር አፅንዖት በመስጠት በዘርፎች ውስጥ ጠንካራ ትብብር በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕይወት አድን መድኃኒቶችን ውጤታማነት ለመጠበቅ አብረን መስራት አለብን ያሉት ሚኒስትሯ፤ አዲሱ የድርጊት መርሃ ግብር ክትትልን ለማሻሻል፣ ምክንያታዊ የመድኃኒት አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ላቦራቶሪዎችን ለማጠናከር እና የህዝብ ግንዛቤን ለማስፋት የብዙ ዘርፍ ጥረቶችን እንደሚመራም አክለዋል።
የአካባቢ ጤና የመፍትሔው ቁልፍ አካል ነው፤ ያሉት የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሌሊሴ ነሜ፣ ብክለትን ለመቀነስ እና ሥነ-ምህዳሮችን ለመጠበቅ የተቀናጀ እርምጃ አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።