3ኛው ዙር የAVoHC-SURGE ስልጠና በመካሄድ ላይ ይገኛል

ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጡ ቡድኖችን ማጠናከርና መጠቀም ላይ የሚያተኩረው የአፍሪካ ፈቃደኛ የጤና ሠራተኞች ‘African Volunteers Health Corps _ Strengthening & Utilizing Response Groups for Emergencies (AVoHC-SURGE) ስልጠና በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የተለያዩ የሴክተር ባለሙያዎችን ያካተተው የ ‘AVoHC-SURGE’ ስልጠና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የፌደራል ፖሊስ ጤና መምሪያ ኃላፊ፣ የጦር ኃይሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ፣ የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ እንዲሁም ሌሎች ኃላፊዎች በተገኙበት ታህሳስ 5/2017 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል።
ይህ ስልጠና በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ በፊት በነበሩት ሁለት ዙር ስልጠናዎች 190 ባለሙያዎች ስልጠናውን በተሳካ መልኩ አጠናቀው ወደ ተግባር ገብተዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ስልጠናውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፡- በኢትዮጵያ የተለያዩ የህብረተሰብ ጤና ችግሮችን ለመከላከል፣ ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት ያላትን አቅም በማሳደግ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለሚከሰቱ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ በመስጠት እና ተጽዕኖ በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት መፈጸማቸውን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሀገራዊ አቅም እና ብቃት ለማጎልበት በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ይህ 3ኛው ዙር የ ‘AVoHC-SURGE’ ስልጠናም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የፕሮግራሙን ዓላማ ስገልጹ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የጤና ክስተቶች በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እና መቀነስ፡ በአደጋዎች ወቅት መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ ድንገተኛ የጤና ክስተቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ እንዲሁም ሁሉ አቀፍ የጤና ደህንነት ተግባራትን በማከናወን ሀገራዊ አቅም ለማጠናከር መሆኑን አስረድተው ፤ አያይዘውም የድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት (Public Health Emergency Operations Centers) አደረጃጀት በአገር-አቀፍ ደረጃ እና በሁሉም ክልሎች ተጠናክረው ወደስራ በመግባታቸው የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ስከሰቱ ምላሽ በመስጠት እና በማስተባበር ማዕከላቱ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስተመጨረሻም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ላሳዩት ድጋፍ እንዲሁም ይህንን ስልጠና እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት የባለፉት ሁለት ዙር ስልጠናዎች የዘርፈ ብዙ ባለሙያዎች ማለትም የላቦራቶሪ፣ ኤፒዲሚዮሎጂ፣ ኤንቲሞሎጂ፣ የእንስሳት ሕክምና፣ የመረጃ አስተዳደር፣ የአቅርቦት፣ የማህበራዊ ሳይንስ እና ሌሎች ባለሙያዎች የተሳተፋ ሲሆን ከስልጠናዎቹም በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በተከሰቱ የወባና ኮሌራ ወረርሽኞች ምላሽ ሥራዎች ላይ ብቃታቸውን አስመስክረው ዉጤታማ ሥራ መሥራታቸዉን እና ከሌሎች የድንገተኛ ጤና ምላሽ ሰጪ ቡድኖች ጋር ማቀናጀት ለድንገተኛ ጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና ክትትል ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዶ/ር አብርሃም ተፈራ፤ የጦር ኃይሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብ/ጄ ዶ/ር ኃይሉ እንደሻው በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የስልጠናውን ወሳኝ ጠቀሜታዎችን ገልፀው ከሀገር አልፎ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የጤና ክስተቶች ሲኖሩ ለጎሮቤት ሀገሮች ጭምር በትብብር የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ለመስጠት ያላትን አቅም የሚያጐለብት መሆኑን ጠቁመዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮዽያ የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ ቡድን ተወካይ የሆኑት አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው ስለ ስልጠናው ዓላማ እና አጠቃላይ ይዘት ማብራርያ በመስጠት የትብበር ሥራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል ።