3ኛው ዙር የFrontline-FETP- VPD Track ሰልጣኞች ተመረቁ

3ኛው ዙር የመሰረታዊ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Frontline-FETP- VPD Track) ሰልጣኝ የጤና ባለሙያዎች ተመረቁ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የወረዳ ጤና ተቋማት የተውጣጡና ለ3 ወራት መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Frontline-FETP-VPD Track) ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የክትባት መርሃ ግብር (Expanded Program on Immunization /EPI) ባለሙያዎች ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ተመረቁ።

የስልጠናው ዋና ዓላማ የጤና ባለሙያዎችን የእውቀትና የክህሎት አቅም በማሳደግ፣ በክትባት የምንከላከላቸውን በሽታዎች የቅኝት እና የልየታ ስራዎችን በማከናወን ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሕብረተሰቡን ጤና የማስጠበቅ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በምርቃት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እነዚህን መሰል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተቁመው፣ በመሰረታዊ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግና በማጎልበት በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱን የልህቀት ማዕከል ከማድረግ ጎን ለጎን የባለሙያዎችን አቅም ከፍ በማድረግና የሁሉንም ቅንጅታዊ ስራዎች በማሳደግ ለሌሎች አገራት ተምሳሊት የሆነ ውጤታማ ስራ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩም አያይዘው ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት፣ ክህሎት እና ልምድ በመጠቀም በጋራና በቅንጅት ሕብረተሰቡ ዘንድ ሊደርስ የሚችል ከፍተኛ ለውጥ ማሳየት የሚችል ተግባር ማከናወን እንደሚገባቸውና፣ ለዚህም የኢንስቲትዩቱ ድጋፍ እና ቁርጠኝነት ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል::
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የክትባት መርሃ ግብር ባለሙዎች በቅንጅት የሰለጠኑበት የስልጠና ፕሮግራም በአይነቱ ለየት ያለና የመጀመሪያ መሆኑን እንዲሁም ባለሙያዎች ያአገኙትን እውቀትና ግንዛቤ በመጠቀም የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ባለሙያ እና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ጃፋር ከዛሊ በበኩላቸው ለሶስት ወራት የአቅም ግንባታ ስልጠና የተከታተሉት የጤና ባለሙያዎች በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች አስመልክቶ የቅኝት፣ የልየታ እና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ላይ የተሻለ የእውቀት፣ የክሕሎትና የግንዛቤ አቅምን እንዲያጎለብቱ ስልጠናው በጥልቀት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ደግሰው ደርሶ ጤና ጥበቃ የክትባት አገልግሎት ተወካይና ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የአፍኔት(AFENET) ድርጅት ሪጂናል አስተባባሪ ስልጠናውን አስመልክቶ የየራሳቸውን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን አፍሪካ ሲዲሲ (US Centers for Disease Control and Prevention/CDC) እና አፍኔት (African Field Epidemiology Network /AFENET) የቴክኔክና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከስልጠናው አስተባባሪ መረዳት ተችሏል፡፡
ሰልጣኝ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው በስራ ቦታቸው የተሰጧቸውን የፊልድ ፕሮጀክቶች አጠናቀው በጽሁፍና በግንባር ገለጻ (Presentation) አማካኝነት መገምገማቸውን ጠቅሰው፣ ስልጠናው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስመዝገብና ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን የዕለት ከዕለት የጤና አገልግሎቶች በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ስልጠናውን በብቃት ተከታትለው ያጠናቀቁና በአማካይ 70 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 14 የኮርሱ ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።