“Community PHEM” ኢኒቬቲቭ ላይ ምክክር ተካሄደ

የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት ቅኝትና ምላሽ ስራዎችን በማህበረሰብ ደረጃ ለመተግበር የሚያስችል “Community PHEM” የተሰኘው ኢኒሸቲቭ ላይ ምክክር ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የ”Community PHEM ” ኢኒሸቲቭን በማህበረሰብ ደረጃ ለማስፈጸም የሚያስችል ምክክር አካሄደ።
ምክክሩ ከክልል ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪዎች፣ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተሮች እና የጤና ትምህርት እና ተግባቦት ባለሙያዎች ጋር የተካሄደ ሲሆን በማህበረሰብ ደረጃ የድንገተኛ ጤና አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ አቅም ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በመርሀግብሩ ላይ ኢኒሼቲቩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነትና ምላሽ ኢኒሸቲቭ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ከማህበረሰብ ጀምሮ በቀላሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የበሽታ ቅኝት ስርዓትን ማጠናከር እና የባለሙያዎችን አቅም መገንባት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። እንዲሁም ከዚህ ቀደም ሲተገበር ከነበረው የጤና ኤክስቴንሽን መርሀግብር ጋር ተባብሮ እና አቀናጅቶ መስራት ለሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ስኬት መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የጤናሚኒስቴር የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ እስራኤል አታሮ በበኩላቸው ማህበረሰብ ተኮር አቀራረብ በድንገተኛ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ላይ ያለውን ወሳኝ ሚና በመግለጽ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በዚህ ሂደት ውስጥ ቁልፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ህብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት የ”Community PHEM ” ኢኒሼቲቭ በማህበረሰብ ደረጃ ያለውን የአደጋ መለየትና ፈጣን ምላሽ አቅም ለማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ የፈጣን ምላሽ ቡድን አስተዳደር ዲቪዥን ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አስራት ይህ የ”Community PHEM ” ስለሚኖው የአተገባበር ሂደትን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ፍሬምወርክ (Framework) በማቅረብ ስለቀጣይ ስራዎች፣ የአፈፃፀም ሂደት እና የስራ ድርሻዎችን በዝርዝር አስረድተዋል።
ምክክሩ ላይ ተሳታፊዎች የ”Community PHEM ” ኢኒሼቲቭን በክልል፣ በወረዳ እና በጤና ኬላ ደረጃ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የተቀናጁ የስራ አቅጣጫዎችን ማካተቱን እና የማህበረሰብ አቅም ማጎልበት፣ የመረጃ ስርዓት ማሻሻል እና ትብብር ማጠናከር እንደሚያስችል አስተያየት ሰጥተዋል።