ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በስብሰባው መክፈቻ ላይ በመገኘት ባስተላለፋት መልዕክት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ጤና ደንብ ፈራሚ ሀገር አንደመሆኗ መጠን የመጀመሪያውን ሁሉንም ሴክተሮች የሚያሳትፈውን በራስ የሚዘጋጀውን የጥምር የውጭ ግምገማ (JEE) እ.ኢ.አ. በ2016 ማከናወኗን አውስተው ይህ ሁለተኛው ግምገማ ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ እሳቤዎችን በተመለከተ ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ አቅምን ለማወቅ እና የሀገሪቷን ደረጃ ለማመላከት ብሎም በሚገኘው ውጤት ላይ በመመርኮዝ ቀጣይ የዓለም አቀፋን የጤና ደህንነት መርሃግብር ለመተግበር የሚቻልበትን ሁኔታዎች ለማጠናከር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የጤና ሥራዎች የበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በጋራ ተናቦ መስራትና መተጋገዝን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም ተቋማት ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ እንደነበረ ሁሉ አሁንም በጋራ እንዲሠሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚም የዓለም አቀፉንና የሀገራቷን የጤና ደህንነት መርሀ ግብር የተሳካና ውጤታማ ይሆን ዘንድ በገንዘብ፤ በማቴሪያልና የቴክኒካል እርዳታ ለሚያደርጉ ተቋማት በሙሉ ምስጋቸውን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ፈይሣ ረጋሳ የኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ጤና ደንብ መርሀ ግብር ተጠሪ በበኩላቸው ባስተላለፋት መልዕክት ሁሉም ሴክተሮች ተገቢውን እና በቂ መረጀ በመስጠት እንዲሳተፋ ጥሪያቸውን አቅርበው በቀጣይ ሶስት ቀናት በሚከናወኑ ሥራዎች ላይም ባለሙያዎችን በመመደብ ሙያዊ አስተዋፅኦአቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ፈይሣ አያይዘውም የሀገሪቷን የጤና ደህንነት አቅም ግንባታ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ለተሳታፊዎቹ ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ለሶስት ቀናት ያህል ሲካሄድ በሚቆየው በዚህ የሀገሪቷ የጤና ደህንነት የራስ አቅም ግምገማ ስብሰባ ላይ ከተለያዩ መንግታዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስብሰባውን በመካፈል ላይ ይገኛሉ፡፡